የተመድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት “በኬንያ-ሶማሊያ የድንበር ውዝግብ” ጉዳይ ላይ ውሳኔ ሊያሳልፍ ነው
የሚሰጠው ብይን የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ እንዳያደሻክረው ተሰግቷል
ኬንያ እና ሶማሊያ የሚወዛገቡበት ስፍራ የነዳጅ እና የዘይት ክምችት እንደያዘ ይታመናል
የተባበሩት መንግሰታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኬንያ እና ሶማሊያ መካከል ባለው የድንበር ውዝግብ ጉዳይ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተገለጸ።
ውሳኔው በቀጠናው ያለውን “የሁለትዮሽ ትስስር እና የኢነርጂ ኤሌክትሪክ ሃይልን ማውጣት ከግምት ያስገባ ነው”ም ነው የተባለው።
- ኬንያ ከሶማሊያ ጋር የገባችበትን የድንበር ውዝግብ ጉዳይ ከሚመለከተው ዓለም አቀፍ የፍርድ ሂደት ራሷን አገለለች
- ሶማሊያና ኬንያ ወደ ንግግር እንዲመጡ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር አሳሰቡ
“የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት (ICJ) ከሰባት ዓመታት በፊት በሞቃዲሾ በቀረበ ክስ መሰረት የመጨረሻ ቃሉን ይሰጣል” ሲልም ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል።
በአሜሪካዊው ዳኛ ጆአን ዶንጉሁ የሚመራው 15 ዳኞች ያካተተው ቡድን በዛሬው ዕለት በዘ-ሄግ የመጨረሻ ብይን ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል።
በሀገራቱ መካከል በቆየው መካሰስ ምክንያት የሀገራቱ ሉዓላዊነት፣ የባሕር ሀብት እና የወደፊት ግንኙነት አደጋ ላይ እንደቆየ ይታወቃል።
ኬንያ ቀደም ሲል ዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት (አይ.ሲ.ጄ) አድሏዊ አድርጋ በመቃወም የፍርድ ቤቱን አስገዳጅ ስልጣን እንደማትቀበል አስታውቃለች።
ዋናው የሃገራቱ መከራከሪያ ጉዳይ የጋራ የባህር ድንበር፤ በባህር ዳርቻ ላይ ከሚገናኙበት ቦታ መውሰድ ያለበት አቅጣጫ ወዴት መሆን አለበት የሚል ነው።
ሶማሊያ፡ ድንበሩ የመሬት ድንበሯን አቅጣጫ በመከተል ወደ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ መጓዝ አለበት ትላለች።
እንደፈረንጆቹ ከ1979 ጀምሮ ሉዓላዊነቷን ጠብቃ እና እስከ 200 የባህር ማይልስ ክልል ውስጥ የኢኮኖሚ ዞን አውጃ ስትንቀሳቀስ እንደቆየች የምታነሳው ኬንያ፤ በተቃራኒው ድንበሯ ቀጥታ መስመር በስተ ምሥራቅ እንደሚሄድ ትናገራለች።
ኬንያ እና ሶማሊያ አሁን የሚወዛገቡበት 100 ሺህ ካሬ ሜትር የሚገመት ስፍራ የነዳጅ እና የዘይት ክምችት እንደያዘ ይታመናል።
ናይሮቢ በስፍራው የጣልያን የኢነርጂ ግዙፍ ኩባንያዎች እንዲሰማሩ ብትፈቅድም ሶማሊያ ተቃውሞዋን በመግለጽ ላይ ትገኛለች።
ሶማሊያ እና ኬንያ ያለቸውን የድንበር ውዝግብ በሁለትዮሽ ድረድሮች ለመፍታት እንደፈረንጆቹ በ2009 ከስምምነት መድረሳቸው የሚታወስ ነው።
ሀገራቱ እንደፈረንጆቹ በ2014 ሁለት የምክክር መድረኮች ያካሄዱ ቢሆንም የታየው ውጤት የተጠበቀውን ያክል እንዳልሆነ ይነገራል።
በተመሳሳይ ዓመት የኬንያ ባለስልጠናት የድንበር ውዝግቡ “የደህንነት ስጋት” አድርገው በማቅረባቸው፤ ሀገራቱ በጉዳዩ ላይ የጀመሩት ምክክር ሊቋረጥ ችሏል።
የሁለትዮሽ ድርድሩ መቋረጡ ተከትሎም ሶማሊያ “የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ሙከራ የትም አላደረሰም” በሚል አጅንዳውን ወደ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በመውሰዷ ምክንያት እስካሁን ድረስ ሲንከባለል ቆይቷል።
እንደፈረንጆቹ 2019 ሶማሊያ በሚያወዛግብ ስፋራ ላይ የሚገኝ ነዳጅ እየሸጠች ነው በሚል፤ ኬንያ በሞቃዲሾ የነበረውን አምባሳደሯን ማስወጣቷም የሚታወስ ነው።
በወቅቱ ድርጊቱን “ህገ -ወጥነት” ነው በማለትም ነበር የጠራችው ኬንያ።
በዛሬው ዕለት የሚሰጠው ብይንም ታድያ በሀገራቱ መካከል መላላት የጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ እንዳያደሻክረው የፖለቲካ ልሂቃን ያላቸውን ስጋት በመግለጽ ላይ ናቸው።
ኬንያ በአሚሶም ስር በመሆን አልሻባብን በመወጋት ከፍተኛ መስወእትነት እየከፈሉ እና ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ከሚገኙ የቀጠናው ሀገራት መሆኗ ይታቃል።