በሰሜን አሜሪካ ሜክሲኮ የተከሰተውን ሙሉ የጸሀይ ግርዶሽ የአየር ንብረት ሁኔታው የፈቀደላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተመልክተውታል
በሰሜን አሜሪካ ከሰባት አመት በኋላ በሜክሲኮ ትናንት ምሽት የተከሰተውን ሙሉ የጸሀይ ግርዶሽ የአየር ንብረት ሁኔታው የፈቀደላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተመልክተውታል።
የመጀመሪያው ሙሉ የጸሀይ ግርጆሽ የታየው በሜክሲኮዋ የውቅያኖስ ዳር ከተማ ማዛትላን ከተማ ነው። ይህን አስገራሚ ሁነት ለማየት በርካቶች ለ10 ሰአታት የፈጀ የመኪና ጉዞ አድርገዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለዚሁ አላማ የተሰራውን መነጽር አድርገው አስገራሚውን ተፈጥሮአዊ ክስተት በጉጉት ተከታትለዋል።
ጸሀይ ሙሉ በመሉ በጨረቃ ስትሸፈን ወይም ሙሉ የሚባለው የጸሀይ ግርዶሽ ሲከሰት ተመልካቹ ከፍተኛ ጩኸት እና ጭብጨባ አሰምቷል።
ሰማዩ ጥርት ባለበት እና ግርዶሹ በሚታይበት ቀጣና ያሉ ተመልካቾች፣ጸሀይዋ በቀስታ በጨረቃ ተጋርዳ ሲጨልም ለማየት ችለዋል።ሙሉ የጸሀይ ግርዶሹ የቆየው ለ4 1/2 ደቂቃ ነው።
ጨረቃ ጸሀይን በከፊል የጋረደችበት ወይም ከፊል ግርዶሽ በበርካታ የአሜሪካ አህጉር አካባቢዎች ተስተውሏል።
የግርዶሽ አድናቂዎች ሙሉ የጸሀይ ግርዶሽ በታየባቸው ከሜክሲኮ ፓሲፊክ ጫፍ በቴክሳስ በኩል እስከ ካናዳ ድረስ ተሰብስበው ነበር።
ይህ 4 1/2 ደቂቃ የፈጀው ሙሉ የጸሀይ ግርዶሽ በ2017 በአሜሪካ ጠረፍ ቦታዎች ታይቶ ከነበረው ግርዶሽ በጊዜ እርዝማኔ ይበልጣል።
የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ማዕከል እንደገለጸው ከሆነ ሙሉ ግርዶሽ በየትኛው ቦታ ከ10 ሰከንድ እስከ 7 1/2 ደቂቃ ድረስ ይቆያል።
ሳን አንቶኒዮ፣ ኦስቲን ኤንድ ዴላስ፣ ቴክሳስ፣ ኢንዲያናፖሊስ፣ ኢንዲያና፣ ኦሀዮ፣ ኢሪ፣ ፔንሲልቫኒያ፣ ኒያጋራ ፎልስ፣ ኒው ዮርክ፣ ኦንታሪዎ፣ ሞንትሪል እና ኪዩቤክ ከተሞች በሙሉ ግርዶሽ ቀጣና ከሚገኙት ከተሞች መካከል ናቸው።
ሙሉ ግርዶሹ በታየበት ቀጣና ከ32 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን የሚኖሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አምስት ሚሊዮን ሰው ግርዶሹን ማየቱን የፌደራል ባለስልጣናት ተናግረዋል።
በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ቀለበታዊ የሚባል የጸሀይ ግርዶሽ ተከስቶ በርካታ ቦታዎች በጨለማ የዋጡበት ክስተት ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ዋናው የጸሀይ ግርዶሽ ከ140 ከመታት በኋላ እንደሚከሰት ባለሙያዎች ተናግረዋል።