አሜሪካ፣ ቻይና በኒውክሌር መሳሪያ አደጋ ጉዳይ ለመወያየት ፍላጎት እያሳየች አይደለም አለች
ቻይና ከአሜሪካ ጋር የሚደረግ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ድርድርን ለረጅም ጊዜ ስትቃወም ቆይታለች
አሜሪካ ከ60 ዓመታት በፊት የነበረውን የኩባ ሚሳይል ቀውስ እንዳይመጣ ስጋት እንዳላትም ገልጻለች
ቻይና የኒውክሌር ጦር መሳሪያን አደጋ ለመቀነስ በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ ለመወያየት ፍላጎት እያሳየች አይደለም ሲሉ የአሜሪካ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ምክትል ዋና ጸሀፊ አሌክሳንድራ ቤል ተናገሩ፡፡
ምክትል ዋና ጸሃፊው ይህንን ያሉት የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ባለፈው ወር ቤጂንግ ራሷን ከኒውክሌር ጥቃት ለመከለካል የሚያስችላት ስትራተጂካዊ አቅም ታጠናክራለች ሲሉ መደመጣቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ፔንታጎን ቻይና ከፍተኛ የኒውክሌር ሃይሏን እያሰፋች በፈረንጆቹ 2030፣ 1ሺ የኒውክሌር የጦር ራሶች እንዲኖሯት እየተንቀሳቀሰች ነው ማለቱም የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ቤጂንግ ከዋሽንግተን ጋር የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ድርድርን ለረጅም ጊዜ ስትቃወም ቆይታለች፡፡ይህ ደግሞ አሜሪካ ቀድሞውንም የግዙፍ የጦር መሳሪያዎች ባለቤት ናት በሚል እንደሆነ ይገለጻል፡፡
የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ምክትል ዋና ጸሀፊ አሌክሳንድራ ቤል ግን የቻይና አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ ይሞግታሉ፤“ከ60 ዓመታት በፊት የነበረውን የኩባ ሚሳዔል ቀውስ” በማስታወስ፡፡
አሌክሳንድራ ቤል ለአትላንቲክ ካውንስል እንደተናገሩት ምንም እንኳን የአሜሪካ ጥረት ቢደረግም ዋሽንግተን እና ቤጂንግ አሁንም በጉዳዩ ላይ መነጋገር አልጀመሩም።
ዋሽንግተን ከሩሲያ ጋር ለብዙ አስርተ ዓመታት እንዲህ ዓይነት ውይይት እንዳደረገች የገለጹት አሌክሳንድራ ቤል “እንደ መጀመሪያው እርምጃ፣ ስለ አንዳችን የሌላውን ዶክትሪን፣ ስለ ቀውስ ኮሚዩኒኬሽን እና ስለ ቀውስ አስተዳደር ከእነሱ ጋር ለመነጋገር እንፈልጋለን”ም ብለዋል።
"አሁን የኩባ ሚሳኤል ቀውስ 60ኛ አመት ላይ ነን። በጠረጴዛው ላይ መገኘት እንደሚያስፈልገን ለማወቅ መድገም አያስፈልገንም" ሲሉም አክለዋል ቤል እንደፈረንጆቹ 1962 የነበረውን የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ፡፡
የፈረንጆቹ 1962 በኩባ የሶቪየት ህብረት ህብረት ሚሳዔሎች ተገኝተዋል በሚል አሜሪካና ሶቪየት ህብርት ወደ ጦር መማዘዝ ተቃረቡበት አደገኛ ወቅት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ባለፈው አመት በቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ እና በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን መካከል በነበረው የስልክ ውይይት "በስትራቴጂካዊ መረጋጋት ላይ ውይይት ለማድረግ የተስማሙበት ነበር" ያሉት ደግሞ የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ናቸው።
ነገር ግን ዢ በጥቅምት ወር በኮሚኒስት ፓርቲ ኮንግረስ ላይ ቻይና ስትራቴጅካዊ መከላከያዋን እንደምታጠናክር ምልክት ሰጥተዋል፤ ይህ ቃል የኑክሌር ጦር መሳሪያን ለመግለጽ ብዙ ጊዜ መጠቀማቸው ደግሞ ለጉዳዩ ያላቸው ፍላጎት የሚያመለካት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሌላው በአትላንቲክ ካውንስል ላይ ንግግር ያደረጉት የአሜሪካ የኑክሌር እና የጅምላ ጥፋት ፖሊሲ መከላከያ ምክትል ጸሃፊ ሪቻርድ ጆንሰን በበኩላቸው አሜሪካ ከጦር መሳሪያ ብዛት ይልቅ "በተጨማሪ መሰረታዊ ነገሮች" ላይ ከቻይና ጋር ልውውጥ ለመጀመር ፍልጎት አላት ሲሉ ተደምጠዋል ።
"ቤጂንግ የምታቀርበው መከራከሪያ ይህ ከሆነ ስለ ቁጥሮች ለመወያየት አንጠይቅም፤ እኛ እያልን ነው አላስፈላጊ ቀውሶች እንዳይኖሩን እንነጋገር ነው"ም ብለዋል፡፡
ጆንሰን አክለውም ቤጂንግ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ላለመሳተፍ የምትመርጥ ከሆነ በዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በኩል የፕሉቶኒየም ክምችቷን ለሲቪል ዓላማ በማወጅ የኒውክሌር አሰባሰብን በተመለከተ አንዳንድ ግልጽነትን ማሳየት ትችላለች ሲሉም ሌላው አማራጭ ጠቁመዋል፡፡