ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ/ህወሓት/ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር እንደማይዋሃድ አስታወቀ
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ/ህወሓት/ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር እንደማይዋሃድ ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡
ድርጅቱ ለሁለት ቀናት ያካሔደውን ጉባኤ ዛሬ ሲያጠናቅቅ ባወጣው የአቋም መግለጫ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር የዓላማና የመስመር ልዩነት ስላለው እንደማይዋሃድ አስታውቋል።
ከፌዴራል መንግስት ጋር የሚኖረው ግንኙነትም ህግና ህገ-መንግስትን መሰረት ያደረገ እንደሚሆን ያመለከተው መግለጫው ከዚህ ውጭ የሚኖር እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደማይኖረው አመልክቷል።
ኢህአደግን የመሰረቱ የአራት ድርጅቶችን የጋራ ሀብት ህግና ስርአትን በተከተለ መንገድ ድርሻውን ለማግኘት እንደሚሰራም በአቋም መግለጫው አስታውቋል።
የኢህአዴግን መፍረስ ተከትሎ ህወሓት ከሌሎች ፈዴራላዊ ሀይሎች ጋር በፎረም፣በጥምረትና በግንባር ደረጃ ስትራተጂካዊ ግንኙነት ለመመስረት መወሰኑንም ገልጿል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
ምንጭ፡- ኢዜአ