ከህወሓት ጋር ለሚደረገው ድርድር በፌዴራል መንግስት የተደራዳሪ ቡድን ተሰየመ
የብልፅግና ፓርቲ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር ለመፍታት የሰላም ድርድሮች እንዲደረጉ ውሳኔ አሳለፈ
የሰላም ሂደቱ በአፍሪካ ህብረት መሪነትና አስተባባሪነት እንዲከናወንም አቋም ተይዘዋል
የብልፅግና ፓርቲ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር ለመፍታት የሰላም ድርድሮች እንዲደረጉ ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ።
የብልፅግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የፍትሕ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በሰጡት መግለጫ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በማቆም ያለው የሰላም አማራጭ እንዲሞከር ተወስኗል ማሌቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመሆኑም የሰላም አማራጭ እንዲሞከር መወሰኑን ገልጸው፤ ኮሚቴዎቹ የሰላም አማራጩ የመጨረሻ ግቡ እንዲሁም የሚመራበትን መርሆና ማዕቀፍ በግልፅ ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል።
የሰላም ንግግሩ ህገ-መንግስታዊነትን የሚያስከብር እንዲሆን አፅንኦት መሰጠቱን ገልጸው፤ የሰላም ንግግሩ ሂደትም ሆነ ውጤቱ የአገር ሉዓላዊነትን ጨምሮ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከበር እንዲሆን መወሰኑን አብራርተዋል።
የሰላም ሂደቱ በአፍሪካ ህብረት መሪነትና አስተባባሪነት እንዲከናወንም አቋም ይዘዋል ብለዋል።
ነገር ግን በሌላኛው ወገን የሰላም ጥረቱን የሚያደናቅፍና አገርን የሚጎዳ እርምጃ ቢኖር መንግሥት የኃይል እርምጃ እንደሚወስድ አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል።
ለዚህም የአገር መከላከያ ሠራዊቱ በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆን መወሰኑን ተናግረዋል።
በፌዴራል መንግስት በኩል የሰላም ተደራዳሪ ቡድን መሰየሙን ያስታወቁ ሲሆን፤ በምክትለ ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው የቡድኑ አባላትም የሚከተሉት ናቸው፡-
1ኛ. አቶ ደመቀ መኮንን........ሰብሳቢ
2ኛ. ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዎስ.....አባል
3ኛ. አቶ ተመስገን ጥሩነህ......አባል
4ኛ. አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር....አባል
5ኛ. አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን.....አባል
6ኛ. ሌ/ል ጀኔራል ብርሀኑ በቀለ....አባል
7ኛ. ዶ/ር ጌታቸው ጀምበር.........አባል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሳምንት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበረቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማምጣት የሚያስችል ኮሚቴ መቋቋሙን መግለፃቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽ፤ ከህወሓት ጋር ለመደራደር ኮሚቴ ተቋቁሞ አስፈላጊ ሁኔታዎችን እየተያደረጉ ነውም ብለዋል።
ህወሓት በበኩሉ በኬንያ መንግስት በተጠራው ድርድር የሚሳተፍ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን በሊቀ መንበሩ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ማስታወቁ ይታወሳል።