ከህወሓት ጋር የሚደረገው ድርድር በአፍሪካ ህብረት ስር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገለጸ
ህወሓት ከዚህ በፊት ከፌደራል መንግስት ጋር የሚደረገው ድርድር የኬንያ ትምራው ማለቱ ይታወሳል
በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ያሉ 12 ሺህ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ስራ መጀመሩ ተገልጿል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ላይ ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሀ ሙሌት እና የፌደራል መንግስት ከህወሀት ጋር የሚያደርገው ድርድር ዋነኞቹ ናቸው።
አምባሳደር መልስ ዓለም የታላቁ ህዳሴው ግድብ ሶስተኛ ዙር ውሀ ሙሌትን በሚመለከት የግድቡ ውሀ ሙሌት ተጀምሯል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም "የግድቡ ግንባታ እየተካሄደ ነው፣ ውሀ ሙሌቱም የዚህ አንድ አካል ሆኖ ይቀጥላል " ሲሉ ተናግረዋል።
በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት ህይወታቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ እየመሩ ያሉ ኢትዮጽያውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራው በግማሽ መሳካቱንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
በአፍሪካ ሀገራት እስር ቤቶች ያሉ 12 ሺህ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራው ዛሬ ይጀመራልም ብለዋል።
102 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የመመለስ ስራው እስካሁን 126 በረራዎችን በማድረግ 50 ሺህ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን አምባሳደር መለስ ገልጸዋል።
አምባሳደር መለስ ድርድርን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም፤ በህወሓት እና የፌደራል መንግስት የሚያደርጉት ድርድር በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ይካሄዳል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድን ሁሴን በትናንትናው ዕለት ከህወሀት ጋር የሚደራደረው የፌደራል መንግስት ኮሚቴ ስራ ጀምሯል ሲሉ በትዊተር ገጻቸው መናገራቸው ይታወሳል።
ኮሚቴው በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለሚካሄደው የሰላም ውይይት የራሱን የአሰራርና ሥነምግባር አካሄድ ተወያይቶ መወሰኑንም አምባሳደር ሬድዋን ጠቁመዋል፡፡
ኮሚቴው በስሩ ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማደራጃትም ኃላፊነት ተከፋፍሎ ስራውን መጀመሩንም አስታውቀዋል።
ህወሀት ከዚህ በፊት በአፍሪካ ህብረት ወገንተኝነት ላይ ጥያቄ እንዳለው ገልጾ ድርድሩን የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ይምሩት ማለቱ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከወር በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበረቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማምጣት የሚያስችል ኮሚቴ መቋቋሙን መግለፃቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽ፤ ከህወሓት ጋር ለመደራደር ኮሚቴ ተቋቁሞ አስፈላጊ ሁኔታዎችን እየተያደረጉ ነውም ብለዋል።
ህወሓት በበኩሉ በኬንያ መንግስት በተጠራው ድርድር የሚሳተፍ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን በሊቀ መንበሩ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ማስታወቁ ይታወሳል።