አሜሪካን ጨምሮ አምስት ሀገራት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት እንዲቆም ጠየቁ
ሀገራቱ፤ ሁሉም የውጭ ተዋናዮች ይህንን ግጭት የሚያባብሱ ድርጊቶችን ማቆም አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል
ሀገራቱ ባወጡት መግለጫ መንግስት እና ህወሓት በአፍሪካ ህብረት ወደ ሚደረገው ድርድር እንደሚጡም ጠይቀዋል
አሜሪካን ጨምሮ አምስት ሀገራት ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት እንዲቆም ጠየቁ፡፡
አሜሪካ፣አውስትራሊያ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ እና ብሪታኒያ ባወጡት የጋራ መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና ሰብዓዊ ቀውስ መባባስ በእጅጉ አሳስቦናል ብለዋል፡፡
“የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ወታደራዊ ግጭትን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ፣ ጦርነቱ እንዲቆም ስምምነት እንዲደረግ፣ ያልተገደብ ሰብዓዊ አገልግሎት እንዲሰጥ እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት መሪነት ሰላማዊ ድርድር ድርድር እንዲካሄድ እንጠይቃለን”ም ነው ያሉት ሀገራቱ በመግለጫቸው፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የኤርትራ ወታደራዊ ሃይሎች ተሳትፎም እንደሚያወግዙ የገለጹት ሀገራቱ፤ የኤርትራ ኃይሎች ወታደራዊ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያቆሙም ጠይቀዋል፡፡
ሁሉም የውጭ ተዋናዮች ይህንን ግጭት የሚያባብሱ ድርጊቶችን ማቆም አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል፡፡
በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳስባቸው አሜሪካ፣አውስትራሊያ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ እና እንግሊዝ ባወጡት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ሀገራቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት ለተጨማሪ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እና የመብት ጥሰት ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር ነውም ብለዋል፡፡
በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ጥቃት እናወግዛለን ያሉት ሀገራቱ፤ ተፋላሚ ኃይሎቹ ለግጭቱ ምንም አይነት ወታደራዊ መፍትሄ አለመኖሩን ተገንዝበው በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ወደ ሚደረገው ድረድር እንደመጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ፤ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንድታገኝ በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሚደረገው ውይይት ላይ እንዲሳተፉ እንጠይቃለን”ም ነው ያሉት ሀገራቱ በመግለጫቸው፡፡
ማንኛውም ዘላቂ መፍትሄ ለሰብዓዊ መብት ረገጣ እና ጥሰቶች ተጠያቂነትን ማካተት አለበት ሲሉም አሳስበዋል፡፡