የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት እየተሰሙ ያሉ ጭምጭምታዎች
ማንችስተር ዩናይትድ፣ ሊቨርፑል፣ አርሰናል እና ቼልሲ ቀሪ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ጥረታቸውን ቀጥለዋል
የክረምቱ የዝውውር መዝኮት በመጪው አርብ ይዘጋል
የእግሊዝ ቡድኖች የክረምቱ የዝውውር መስኮት ከመዘጋቱ በፊት ተጨዋቾችን ለማስፈረም እያደረጉ የሚገኙትን ጥረት ፍጥነት ጨምረው ቀጥለዋል።
ክለቦች በመዝጊያው ሰአታት የሚፈልጓቸውን ተጫዎቾች ለመግዛት የቤት ስራ ላይ ናቸው ።
የዝውውር ዋጋቸው የተጋነኑ እና አሰልቺ ድርድር የተካሄደባቸው ውሎችም በመጨረሻው ሰአታት እልባት ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ።
የእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ የፊት መስመሩን ለማጠናከር የብሬንትፎርድን በር እያንኳኳ ነው ።
ባለፈው ጥር ወር 100 ሚሊየን ዩሮ ተለጥፎበት የነበረው ኢቫን ቶኒ በ40 ሚሊየን ዩሮ ለማዘዋወር እየተደራደረ ነው ተብሏል ።
የ28 አመቱ አጥቂ የዝውውር ዋጋው የቀነሰው በለንደኑ ክለብ ያለው የውል ጊዜ አንድ አመት ብቻ በመቅረቱ ነው ።
በክረምቱ የዝውውር ገበያ ሻጭም ገዢም የሆነው ቼልሲ ሉካኮን ለናፖሊ አሳልፎ ከሰጠ በኋላ በኔፕልስ ደስተኛ ያልሆነውን ናይጄሪያዊውን አጥቂ ቪክቶር ኦስምሄን ወደ ስታንፎርድ ብሪጅ ለማምጣት ጥረት እያደረገ መሆኑ ተዘግቧል ።
በመጨረሻ ቀናት አዲስ ነገር ጠብቁ ያለው አርሰናል ከአንፊልድ ዳርዊን ኑኔዝን ሊያስኮበልል ይችላል እየተባለ ይገኛል።
የኑኔዝ ዝውውር ያልተጠበቀ ጭምጭምታ በመሆኑ መረጃው ትኩረት የሳበ ሲሆን ኤዲ ኒኪታን ለክሪስታል ፓላስ የሸጠው አርሰናል የሊቨርፑሉን አጥቂ ለማስፈረም ከፍተኛ ፍላጎት አሳይቷል ።
በዝውውር ገበያው በተሳትፎ ተፋዞ የቆየው ሊቨርፑል የጁቬንቱሱን ፌሬድሪኮ ቼዛ በ15 ሚሊየን ዩሮ ማስፈረሙን አረጋግጧል ።
በዌስትሃም ሲፈለግ የነበረው ቴሚ አብርሃም እዛው ጣሊያን ኤሲ ሚላንን ለመቀላቀል በግል ጉዳይ መስማማቱ ተዘግቧል ።
በእንግሊዝ ክለቦች ሲፈለግ የነበረው የባየር ሙኒኩ የመስመር አጥቂ ኪንግስሌይ ኮማን ወደ ሳውድ አረቢያው አል ሂላል ሊያመራ ይችላል ።
ባየር ሙኒክ የአልሂላልን ጥያቄ መቀበሉ ሲነገር ተጫዎቹም ይሁንታውን መስጠቱ ተሰምቷል።
ከነገ በስተያ በሚዘጋው የዝውውር መስኮት በመጨረሻ ደቂቃዎች ያልተጠበቁ ዝውውሮች ሊደረጉ እንደሚችል ይገመታል ።