ሩሲያ ምግብን እንደ “ድብቅ ሚሳዔል” እየተጠቀመችበት ነው- አውሮፓ ህብረት
በአውሮፓ ህብረት ክስ የተበሳጩት የሩሲያ ተወካይ የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባን ረግጠው ወጥተዋል
ህብረቱ አሁን በዓለም ላይ ላለው ቀውስ ሁሉ “ሩሲያ ተጠያቂ መሆኗ” ሊታወቅ ይገባል ብሏል
ሩሲያ የምግብ አቅርቦትን እንደ ‘ድብቅ ሚሳኤል’ እየተጠቀመችበት ነው ሲሉ አውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ቻርለስ ሚሸል፤ ሩሲያ የምግብ አቅርቦትን እንድ ድብቅ ሚሳዔል በመጠቀም በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራትን ለከፋ ድህነት እየዳረገች ነው ሲሉ ከሰዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነው፡፡ ሩሲያ ግን በተወካይዋ አማካኝነት “መሰረተ ቢስ” ስትል ክሱን ውድቅ አድርጋለች፡፡
ይሁን እንጅ ከፍተኛ ክርክር በተስተዋለበት በዚህ ስብሰባ ፤ የአውሮፓ ህብረቱ ፕሬዝዳንት ሩሲያን ያስወቅሳሉ ያሏቸውን መከራከሪያዎች ለጸጥታው ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡
“አምባሳደር ቫዚሊ ኔቤንዢያ እውነት እንነጋገር፤ ክሬምሊን በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራትን ለማደህየት የምግብ አቅርቦትን እንደ ‘ድብቅ ሚሳዔል’ እየተጠቀመችበት ነው” ሲሉም በምክር ቤቱ የነበሩትን ቻርለስ ሚሸል ሞግተዋል፡፡
ሚሸል “የሚያሳዝነው ሩሲያ የጀመረችው ጦርነት በመላው ዓለም እየተዛመተ መሆኑ ነው፤ የምግብ ዋጋ እጅጉን እንዲንር በማድረግ የዓለም ህዝቦች ለድህነት እንዲዳረጉና የተለያዩ ቀጠናዎች እንዲታመሱ እያደረገ ነው ፤ለዚህ ሁሉ ቀውስ ተጠያቂ ሩሲያ መሆኗ ሊታወቅ ይገባል” ሲሉም አክለዋል።
በተጨማሪም በዩከሬኗ ኦዴሳ ደሴት ላይ፤ በሚሊዮን ቶኖች የሚቆጠር የምግብ እህል በሩሲያ የባህር ኃይል ታግቶ እንደሚገኝ በአይኔ አይቻለሁ ብለዋል፡፡
በዚህ መሀል፤ የፕሬዝዳንት ሚሼል ክስ ያበሳጫቸው የሩሲያ ተወካይ ቫሲሊ ኔቤንዚያ የጸጥታው ምክር ቤቱ ስብሳባ ረግጠው መውጣታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቻርለስ ሚሸል ግን፤ ተወካዩ በመውጣት ላይ ሳሉም ቢሆን በሩሲያ ላይ ሲያሰሙት የነበረውን ክስ ማሰማታቸውን ከመቀጠል ያስቆማቸው አልነበረም፡፡
ሚሸል “ከዚህ አዳራሽ መውጣት ትችላለህ፤ ምናልባትም እውነታውን ላለመስማት የተሻለ አመራጭ ሊሆን ይችላል” ሲሉ ከስብስባው አዳራሽ በመውጣት ላይ የነበሩትን ኔቤንዢያን በንግግር ሸንቆጥ ማድረጋቸውም ተሰምቷል፡፡
የስብሰባውን መገባደድ ተከትሎ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደረጉት የሩሲያው ተወካይ ኔቤንዢያ “ቻርለስ ሲያስተጋበው የነበረ ውሸት” ስበስባው ውስጥ እንድቆይ አላስቻለኝም የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡