በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ህወሓት “አቶ ጌታቸው ረዳን ከጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት አንስቻለሁ” አለ
ፓርቲው አቶ ጌታቸውን እንዴትና በማን እንደሚተኩ ከፌዴራል መንግሥትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ይወሰናል ብሏል
ከአስተዳደር ሥልጣናቸው የወረዱ ሰዎች ትግራይን መምራት፣ መወሰንና መወከል አይችሉም ሲል ገልጿል
በእነ ደብረፅዮን ገበረ ሚካኤል ዶ/ር የሚመራው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ቡድን በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ውስጥ የአመራር ማሻሻያ እንዲደረግ መወሰኑን አስታውቋል።
በአጠቃላይ አምስት የጊዜያዊ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላትን፣ ሁለት የቢሮ ሃላፊዎችን እና ሰባት የዞን አስተዳዳሪዎችን ከኃላፊነት ማውረዱን ገልጿል።
ከኃላፊነታቸው የተነሱት ሰዎች ከዛሬ ጀምሮ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር መምራት እንደማይችሉ የገለጸው ፓርቲው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በማ እና እንዴት እንደሚተኩ ከፌደራል መንግስቱ ጋር በመነጋገር እወስናለሁ ነው ያለው፡፡
ፓርቲው ከአስተዳደራዊ ኃላፊነታቸው የተነሱ ሰዎች ከዚህ ቀን ጀምሮ ከተሰጣቸው ኃላፊነት እንዲወጡ ያዘዘ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ ትግራይን መምራት፣ መወሰንና መወከል አይችሉም ሲልም ገልጿል።
መግለጫው ህወሓት በማእከላዊ ኮሚቴው ውሳኔ መሰረት ሰፊ ግምገማ በማድረግ እና ህጋዊ እና ዲሞክራሲያዊ ኮንግረስ በማካሄድ ማካሄዱን አንስቷል፡፡
“ግልጽ ተልዕኮ ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር በጥገኛ ቡድን ተጠልፎ፣ ከተቋቋመለት ዓላማ ወጥቶ፣ ያለ ዕቅድና አቅጣጫ እየተመራ፣ የሥልጣን ጥመኞች ወኪል በመሆን፣ ፍሬ ቢስ ጉዞ እያደረገ ነው” ሲል የጊዜያዊ አስተዳደር አባላቱን ከሷል
ደበረጺዮን የሚመሩት ህውሓት ባቀረበው ሌላኛው ወቀሳ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ምንም እንኳን አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታን የሚያስከብር፣ የማገገም እና የመልሶ ግንባታ ስራዎችን ይጀምራል፣ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተግባራዊ ያደርጋል ፣ለዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ይሰራል እና ለቀጣዩ ምርጫም የተረጋጋ መሰረት ይፈጥራል ተብሎ ቢጠበቅም እነዚህን ህዝባዊ ተልዕኮዎች ትቶ የፖለቲካ ሴራ መሳሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ተደርጓል” ብሏል፡፡
ስለሆነም የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ መስከረም 24 ቀን 2017 ባካሄደው ስብሰባ በቡድኑ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ህወሓትን ወክለው ከአስተዳደራዊ ቦታቸው እንዲነሱ እና በሌሎች የፓርቲው ተወካዮች እንዲተኩ ወስኗል።
በሁለቱ ህውኃቶች መካከል የተፈጠረው ልዩነት እየሰፋ መጥቶ በደብረጽዮን የሚመራው ቡድን ከምርጫ ቦርድ እውቅና ሳያገኝ ካደረገው ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ የጊዜያው አስተዳደሩን አመራሮች ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት አንስቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከዚህ በላፈም በአስተዳደሩ ውስጥ የሚገኙ ሀላፊዎች ፓርቲውን ወክለው ማስተዳደር እና ውሳኔ መስጠት እንደማይችሉ አስታውቆ ነበር፡፡