ዳግም ከተመረጥኩ “የዩክሬኑን ጦርነት በ1 ቀን አስቆማለሁ” ያሉት ትራምፕ ከዜለንስኪ ጋር ተወያዩ
የህዳር ወር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪው ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ጋር “በስልክ ጥሩ ውይይት አድርገናል” ብለዋል
ትራምፕ ዩክሬን በሩሲያ የተያዙባትን የተወሰኑ ግዛቶች ለሞስኮ በመተው ጦርነቱ እንዲቆም ምክረሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል
የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን በድርድር ለማስቆም እንደሚሰሩ በድጋሚ ቃል ገቡ።
በህዳር ወር ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግስት ለመዝለቅ የሚፎካከሩት ትራምፕ በትናንትናው እለት ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ጋር በስልክ ተወያይተዋል።
ዜለንስኪ የግድያ ሙከራ ለተደረገባቸው ትራምፕ አጋርነታቸውን ለማሳየት ስልክ መደወላቸውን ሬውተስ ዘግቧል።
ሪፐብሊካኑ ትራምፕ በዚህ የስልክ ቆይታ “ጥሩ ምክክር” መደረጉን ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው በራሳቸው የማህበራዊ ትስስር ገጽ ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ግን ለትራምፕ መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸውንና ዋሽንግተን ለኬቭ የምታደገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ከመግለጻቸው ውጪ ጦርነቱን ስለማቆም ከትራምፕ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የሚያመላክት መረጃ በኤክስ ገጻቸው ላይ አላጋሩም።
ትራምፕ በህዳር 5ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ካሸነፉ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን በጥር ወር ዋይትሃውስ ከመግባታቸው በፊት እንደሚያስቆሙት መናገራቸው ይታወሳል።
እርሳቸው በስልጣን ላይ ቢሆኑ ኖሮ ክሬምሊን ወደ ዩክሬን በ2022 ጦሯን እንደማታስገባ በማንሳትም የባይደን አስተዳደር ላይ ተደጋጋሚ ትችት ማንሳታቸው አይዘነጋም።
የ78 አመቱ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባለፈው አመት ከሬውተርስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ዩክሬን በሩሲያ የተያዙባትን ግዛቶቿን ለሞስኮ በመተው ጦርነቱን የሚያስቆም የሰላም ስምምነት እንድትደርስ ምክረሃሳብ አቅርበው ነበር።
ኬቭ ግን በሞስኮ የተያዙባትን ግዛቶቿን ሳታስመልስና የሞስኮ ጦር ከዩክሬን ጠቅልሎ ሳይወጣ ጦርነቱ እንደማይቆም በተደጋጋሚ በመግለጽ የትራምፕን ሃሳብ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ባለፈው ወር በስዊዘርላንድ ያቀረቡት የሰላም እቅድም የሩሲያ ወታደሮች ሙሉ በሙሉ ወጥተው ዩክሬን ወደ ድህረ 1991 ድንበሯ እንድትመለስ የሚጠይ ነው።
ትራምፕ “የዩክሬኑን ጦርነት በአንድ ቀን አስቆማለሁ” የሚለው ንግግራቸው ከጦርነቱ ተዋናዮች መብዛትና ውስብስብነት አንጻር ተፈጻሚነቱ አጠራጣሪ ይመስላል።
በየካቲት ወር 2022 ወደ ዩክሬን ጦሯን ያስገባችው ሩሲያ እስካሁን ወደ 20 በመቶ የሚጠጋ የዩክሬንን መሬት በቁጥጥሯ ስር አውላለች።