የትራምፕ የ2025 ፕሮጀክት በጂቡቲ ላይ ትኩረት ያደረገው ለምንድን ነው?
የየመን ሃውቲ ቡድን ጉዳይ የዋሽንግተን እና ስትራቴጂካዊ ፋይዳዋ ከፍተኛ የሆነችውን ትንሽ ሀገር ግንኙነት አሻክሯል
ቻይና በውጭ ሀገር የመጀመሪያ የጦር ሰፈሯን በፈረንጆቹ 2017 በጂቡቲ መክፈቷ ይታወሳል
የምስራቅ አፍሪካዋ ሀገር ጂቡቲ ስፋትና የተፈጥሮ ሀብቷ ዝቅተኛ ቢሆንም መልካምድራዊ አቀማመጧ ግዙፍ ስትራቴጂካዊ አቅም አስገኝቶላታል።
ከአለማችን የባህር ላይ ንግድ ሲሶ የሚሆነው በሚያልፍበት መስመር በቅርብ ርቀት መገኘቷ በርካታ ሀገራት የጦር ሰፈራቸውን በሀገሪቱ እንዲገነቡ አድርጓቸዋል።
ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ አሜሪካ እና ቻይናን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በትንሿ ሀገር የጦር ሰፈራቸውን ገንብተዋል።
"ሪስፖንሲብል ስቴትክራፍት" የተሰኘው የአሜሪካ የኦንላይን መጽሄት ይዞት በወጣው ዘገባ ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግስት የገቡት ዶናልድ ትራምፕ በ"2025 ፕሮጀክት" ውስጥ ለጂቡቲ ትኩረት ሰጥተዋል።
የፕሮጀክቱ ጸሃፊዎች አሜሪካ በጂቡቲ ያላት ተሰሚነት እየተዳከመ መምጣቱን ያምናሉ። ለዚህም የቻይና ተጽዕኖ ማየል አንዱ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ። ቤጂንግ በውጭ ሀገር የመጀመሪያ የጦር ሰፈሯን በ2017 በጂቡቲ መክፈቷ የሚታወስ ነው።
የጂቡቲ እና አሜሪካ ግንኙነት - ሃውቲ
የየመን ሃውቲ ቡድን ጉዳይ የዋሽንግተን እና ስትራቴጂካዊ ፋይዳዋ ከፍተኛ የሆነችውን ትንሽ ሀገር ግንኙነት ማሻከሩን "ሪስፖንሲብል ስቴትክራፍት" አስነብቧል።
አሜሪካ በጂቡቲ ግዛት ውስጥ በመሆን በሃውቲዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ያቀረበችው ጥያቄ ውድቅ መደረጉም የግንኙነቱ መሻከር መንስኤ ነው ተብሏል።
ጂቡቲ ለዋሽንግተን ፈቃዱን ያልሰጠችው ግን ወደ ቤጂንግ በማጋደል ሳይሆን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ምክንያት ነው የሚለው መጽሄቱ፥ የምስራቅ አፍሪኣክዊቷ ሀገር የበርካታ ሀገራት የጦር ሰፈር መገኛ እንደመሆኗ በየሀገራቱ የተለያየ ፍላጎት ላለመጠለፍ ገለልተኛ መሆንን እንደምትመርጥ ያብራራል።
የጦር ሰፈሮቹ እንደ አልቃይዳ አይነት የሽብር ቡድኖችን ለመምታት ጥቅም ላይ ቢውሉ ችግር አይኖረውም፤ እንደ ሃውቲ ያሉ መንግስት ባይሆኑም ከፊል የመንግስት ድርሻ ያላቸውን ቡድኖች ከጂቡቲ ሆኖ መደብደብ ግን ፈተና ይደቅንብኛል በሚል የአሜሪካን ጥያቄ ውድቅ አድርጋዋለች ይላል ዘገባው።
ቻይና በጂቡቲ
ቻይና እንደሌሎቹ የምዕራባውያን ሀገራት በጂቡቲ የጦር ሰፈር የገነባችው በቀይ ባህር የሚጓዙ መርከቦቿን ደህንነት ለማስጠበቅ በሚል ነው።
ቤጂንግ በጂቡቲ ትልቅ አልሚ ስትሆን እንደ ወደብ እና ባቡር ላሉ መሰረተልማቶች በቢሊየን ዶላሮች ታወጣለች።
ጂቡቲ ከአዲስ አበባ ጋር የምትተሳሰርበትና የቻይና ግዙፍ ፕሮጀክት (አንድ ቀበቶ አንድ መንገድ) አካል የሆነው የባቡር መስመር እና የወደብ ልማት 14.4 ቢሊየን ዶላር ወጪ ይደረግበታል።
ቻይናን እንደ ብሄራዊ ስጋት ለሚመለከተው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቤጂንግ በጂቡቲ የምታደርገውን ተሳትፎ በበጎ አያየውም። የአሜሪካ ጀነራሎች የቻይና የጦር ሰፈር እስያዊቷ ሀገር በአፍሪካ ተጽዕኖዋን ለማበርታት እየተጠቀመችበት ነው ያላሉ።
የሶማሊላንድ እውቅና
የጂቡቲን አለመተባበር ያብጠለጠሉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ባለሙያዎች ዋሽኝግተን በቀጠናው ሁነኛ አጋር መሻት አለባት ሲሉ ቆይተዋል።
በ"2025 ፕሮጀክት"ም አሜሪካ በጂቡቲ ዙሪያ ያላትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጣ ለሶማሊላንድ ነጻ ሀገርነት እውቅና መስጠት እንደ አማራጭ ቀርቧል።
ይሁን እንጂ ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠት ቀውስ ሻክሮ የቆየውን ግንኙነታቸውን በትርክ አደራዳሪነት ያለዘቡትን ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዳግም ወደ ውጥረት ውስጥ ሊከት ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ቻይናም አቋሟን ቀይራ ከአሜሪካ በመቀጠል ለሶማሊላንድ እውቅና ልትሰጥ ትችላለች የሚሉ ተንታኞች፥ ጂቡቲም ሆነች ሶማሊላንድ ስጋት ከተሰማቸው ከቻይና ጋር ግንኙነታቸውን ወደማጠንከር ይገባሉ፤ ይህም የቤጂንግን ተጽዕኖ እየጨመረው ይሄዳል በሚል አማራጩ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ።
በሶማሊላንድ የሚታዩ የጎሳ ግጭቶችም ሃርጌሳን የዋሽንግተን አስተማማኝ አጋር የማድረግ ውጥን ችግር ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ይገልጻሉ።
መፍትሄውም የበርካታ ሀገራት የጦር ሰፈሮች መነሃሪያ የሆነችውን ጂቡቲ የገለልተኝነት ፍላጎት ማክበር፤ ከቻይና ጋር ያልተገባ ፉክክር ውስጥ ከመግባት ይልቅ የባህር ላይ ዝርፊያ እና ሽብርተኝነት ላይ በጋራ መስራት መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል።
ፕሮጀክት 2025 ምንድን ነው?
በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የተሳተፉበት የ2025 እቅድ 900 ገጾች ያሉት ሲሆን ዝርዝር የፖሊሲ ጉዳዮችን ያካተተ ነው ተብሏል።
ትራምፕ በድጋሚ ከተመረጠ ሊያተኩርባቸው የሚገቡ ናቸው የተባሉ ጉዳዮችን ያካተተው እቅድ በሄሪቴጅ ፋውንዴሽን ክትትል የሚደረግበት ነው።
ትራምፕ ግን በነሃሴ ወር "ፕሮጀክት 2025 የሚባለውን ጉዳይ ምንም አላውቀውም" ማለታቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ አብዛኞቹን መሰረታዊ የ2025 ፕሮጀክት ሃሳቦች እንደሚቀበሏቸው የተነገረ ሲሆን፥ በጂቡቲ ላይ ስለተያዘው እቅድም እስካሁን በይፋ የተናገሩት ነገር የለም።