የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከሰሜን ኮሪያ ጋር ግንኙነት ካለው ኩባንያ እዳ ደብቀዋል በሚል "ተከሰሱ"
የቀድሞው ፕሬዝደንት ለ25 ዓመታት ያህል ከኩባንያው ጋር ግንኙነት ነበራቸው ተብሏል
ትራምፕ በፕሬዝዳንትነት ዘመቻቸው ወቅት እና ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ሰነዶቹን ለፌደራል ባለስልጣናት እንዲያቀርቡ ይጠበቅባቸው ነበር
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስልጣን ዘመናቸው ከሰሜን ኮሪያ ጋር ታሪካዊ ግንኙነት ካለው ኩባንያ የ19 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ እንዳለባቸው አልገለጹም ተብሏል።
እንደ ፎርብስ መጽሔት ዘገባ ከኒውዮርክ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የተገኙ ሰነዶች ትራምፕ ከዚህ ቀደም ከግዙፉ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያ ዳኢዎ የተበደሩትን ዕዳ አላሳወቁም።
የቀድሞው ፕሬዚደንት ለ25 ዓመታት ያህል ከኩባንያው ጋር ግንኙነት ነበራቸው ተብሏል።
እ.አ.አ በ1990ዎቹ አጋማሽ ፒዮንግያንግ የንግድ ስራ እንዲትሰራ የፈቀደችው ዳኢዎ ብቸኛው የደቡብ ኮሪያ ኩባንያ ነው።
በአንድ ወቅት ዳኢዎ ከትራምፕ ጋር በመተባበር በኒውዮርክ ከተማ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት አቅራቢያ የሚገኘውን ትራምፕ ወርልድ ታወር የተባለውን አፓርታማ መገንባታቸው ተነግሯል።
በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እና በዳኢዎ መካከል የነበረው የንግድ ትብብር ከፈረንጆቹ 1999 እስከ 2007 በደቡብ ኮሪያ የትራምፕ ስም ያላቸውን ስድስት ንብረቶች መቋቋሙም እንዲሁ።
እንደ ፎርብስ ዘገባ ከሆነ ዕዳው የተከሰተው ትራምፕ አንዳንድ የፍቃድ ክፍያዎችን ከዴዎ ጋር ለመካፈል ባደረጉት ስምምነት ነው። በፎርብስ በተገመገሙት ሰነዶች መሠረት እዳው ከ 2011 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ 19 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል።
የወረቀት ሰነዶች መሠረት እ.ኤ.አ. ሀምሌ 2017 ዕዳው ሙሉ በሙሉ ተከፈለ ቢባልም የገንዘቡ ምንጭ አይታወቅም ነው የተባለው።
ፎርብስ እንደዘገበው ብድሩ በትራምፕ ድርጅት ሰነዶች ላይ ሪፖርት የተደረገ ቢሆንም፣ በቀድሞው ፕሬዚዳንት የፋይናንስ መግለጫ ሪፖርቶች ላይ ግን አልተገለጸም።
ትራምፕ በፕሬዝዳንትነት ዘመቻቸው ወቅት እና ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ሰነዶቹን ለፌደራል ባለስልጣናት እንዲያቀርቡ ይጠበቅባቸው ነበር።
በፈረንጆቹ 2016 የትራምፕ የቀድሞ የፋይናንስ ኃላፊ አለን ዌይሰልበርግ "በሰነዶቹ ውስጥ 100 በመቶ ድርሻ ያላቸውን ኩባንያዎች ሁሉንም ዕዳዎች ይፋ አድርገዋል" ብለዋል ።