የትራምፕ አስተዳደር የጉዞ እገዳ ሊጥልባቸው ነው የተባሉ 41 ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
የትራምፕ አስተዳደር ኤርትራ እና ሶማሊያን ጨምሮ በ41 ሀገራት ላይ የጉዞ እገዳ ለማውጣት ሰነድ ማዘጋጀቱ ተነገረ

በከፊል እና ሙሉ ለሙሉ እገዳ የወጣባቸው ሀገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ይከለከላሉ
የትራምፕ አስተዳደር በደርዘን የሚቆጠሩ ሀገራት ዜጎች ላይ የጉዞ ገደቦችን ለማውጣት ዝርዝር ማዘጋጀቱን ሮይተርስ አገኘሁት ያለውን ሰነድ ጠቅሶ ዘግቧል ።
በስደተኛ ላይ ጠንካራ ፖሊሲ የሚያራምዱት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ወደ ሀገራቸው እየመለሷቸው ከሚገኙ ህገ ወጥ ስደተኞች ባለፈ በተለያዩ ሀገራት ዜጎች ላይ የጉዞ ክልከላ አውጥተዋል፡፡
ክልከላ የተላለፈባቸው ሀገራት ዜጎች ለስራ ፣ ለጉብኝት ፣ ጥገኝነት በመጠየቅ እና በተለያዩ የአሜሪካ ቪዛዎች ወደ አሜሪካ ምድር መግባት አይችሉም፡፡
ሮይተርስ ተመለከትኩት ያለው የጉዞ ክልከላ ሰነድ በድምሩ 41 አገሮችን በሶስት የተለያዩ ቡድኖች ይዘረዝራል።
የመጀመሪያው አፍጋኒስታን ፣ ኢራን ፣ ሶሪያ ፣ ኩባ እና ሰሜን ኮሪያ እና ሌሎችንም ጨምሮ በ10 ሀገራት ላይ ሙሉ የቪዛ እገዳ ጥሏል፡፡
በሁለተኛው ረድፍ ኤርትራ፣ ሄይቲ፣ ላኦስ፣ ምያንማር እና ደቡብ ሱዳን ከፊል እገዳዎች የተጣሉባቸው ሲሆን ይህም በቱሪስት ፣ በተማሪ እንዲሁም ሌሎች የስደተኛ ቪዛዎች ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል ነው የተባለው።
በሶስተኛው ቡድን ውስጥ ቤላሩስ፣ ፓኪስታን እና ቱርክሜኒስታንን ጨምሮ በአጠቃላይ 26 ሀገራት መንግስታቸው በ60 ቀናት ውስጥ በኢሜግሬሽን አገልግሎት ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ለመፍታት ጥረት ካላደረገ የከፊል የጉዞ እገዳ እንደሚጣልባቸው ሰነዱ አመላክቷል፡፡
አንድ ስማቸው ያለተገለጸ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ ለሮይተርስ እንደተናገሩት በዝርዝሩ ላይ ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮን ጨምሮ አስተዳደሩ የጉዞ ክልከላ ሰነዱን አላጸደቀውም፡፡
ያሁኑ የጉዞ ክልከላ ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ጊዜያቸው በ2018 በርካታ ሙስሊሞች በሚገኙባቸው 7 ሀገራት ላይ ካወጡት የጉዞ ክልከላ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡
ይህ የትራምፕ የጉዞ እገዳ በ2018 በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከመጽደቁ በፊት ለረጅም ጊዜ ተይዞ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ትራምፕ በጥር 20 ከፈረሟቸው የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዞች መካከል ወደ አሜሪካ የሚገባ ማንኛውም የውጭ ሀገር ዜጋ ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት አለመሆኑን ለማረጋገጥ የተጠናከረ ማጣራት እንዲደረግበት የሚጠይቀው መመሪያ ይጠቀሳል፡፡
በዚህ መመሪያ ላይ በመረጃዎቻቸው ጉድለት እና በተለያዩ ምክንያቶች በከፊል እና ሙሉ ለሙሉ ወደ አሜሪካ ከመግባት መታገድ የሚገባቸውን ሀገራት ዝርዝር ካቢኔው እስከ መጋቢት 21 እንዲያቀርብ ያዛል፡፡