ፖለቲካ
ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያ በተባለው ክስ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በ2016 ለወሲብ ፊልም ተዋናይት የእጅ መንሻ ገንዘብ ከፍለዋል በሚል የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል
ዶናልድ ትራምፕ በወንጀል የተከሰሱ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ናቸው
ለ2024 ምርጫ የሪፐብሊካን እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ፍርድ ቤት ቀርበው በይፋ ክስ ይመሰረትባቸዋል ተብሏል።
የጣት አሻራ እንደሚሰጡና የምስል ማህደራቸው የእስረኞች መረጃ ቋት ውስጥ እንደሚገባም ተነግሯል።
ትራምፕ በፈረንጆቹ 2016 ለወሲብ ፊልም ተዋናይት ስቶርሚ ዳንኤልስ በከፈሉት የእጅ መንሻ ገንዘብ የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
"ንጹህ ነኝ" ሲሉ የሰነበቱት የቀድሞው ፕሬዝዳንት፤ "ጥፋተኛ አይደለሁም" ብለው እንደሚከራከሩ ተናግረዋል።
ትራምፕ ማክሰኞ በጸጥታ ጥበቃ እጃቸውን ሲሰጡ የድጋፍና የተቃውሞ ሰልፍ እንደማይለያቸው ተጠብቋል።
ክስ ለመስማት ማንሀተን ፍርድ ቤት የሚቀርቡት ትራምፕ፤ የይግባኝ ጥያቄ እንደሚያቀርቡም ተነግሯል።
የተከሳሹ ጠበቆች ሂደቱን ያስተጓጉላል በሚል የፍርድ ቤት ውሎን የቪዲዮ፣ የፎቶግራፍ እና የሬዲዮ ስርጭትን ተቃውመዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ክሱ ወይም የወንጀል ውሳኔ ትራምፕን ለፕሬዝዳንትነት ከመወዳደር ህግ እንደማያግዳቸው ተነግሯል።
ዶናልድ ጄ ትራምፕ በወንጀል የተከሰሱ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ናቸው።