ትራምፕ ዛሬ በቁጥጥር ስር ሊውሉ ይችላሉ ተብሏል፤ የአሜሪካ ፖሊስ በተጠንቀቅ ላይ ነው
ትራምፕ ከአንዲት ተዋናይት ጋር የነበራቸውን ግንኙነትን ለመደበቅ ገንዘብ ከፍለዋል በሚል ሊከሰሱ ይችላሉ ተብሏል
ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ “ማክሰኞ ልታሰር እችላለሁ” ብለው መጻፋቸው የሚታወስ ነው
አወዛጋቢው የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ቅዳሜ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ “ማክሰኞ ልታሰር እችላለሁ” ብለው መጻፋቸው የሚታወስ ነው፡፡
"ህገወጡ እና ሙሰኛው የማንሃተን አቃቤ ህግ ቢሮ የፊታችን ማክሰኞ ሊያስረኝ እና ሊከሰኝ ይፈልጋል" ሲሉም ነበር ትራምፕ "ትሩዝ ሶሻል" በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ የጻፉት፡፡
የትራምፕ መልእክት ተከትሎ በአሜሪካ የህግና አስተዳደር ባለስልጠናት ላይ ከፍተኛ ዛቻ እየተሰነዘረ መሆኑም ነው ሮይተርስ የዘገበው፡፡
ዛቻው በዋናነት ያነጣጠረው ትራምፕ ላይ ክስ ይመሰርታሉ ተብለው በሚጠበቁት የማንሃታን አውራጃ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አሊቪን ባራግ ላይ መሆኑም ታውቋል።
ይሁነ እንጅ በትራምፕ ድርጊት ማዘናቸውን የገለጹት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ “"በኒውዮርክ ቢሯችን ላይ ሚደረግ ዛቻ ወይም የህግ የበላይነትን ለማስፈራራት የሚደረጉ ሙከራዎችን አንታገስም" ሲሉ ጽፈዋል፡፡
ትራምፕ ላይ ክስ ለመመስረት በቂ ማስረጃ መኖሩን የሚመረምር የዳኞች ቡድን መቋቋሙን ጭምር ተናግረዋል አቃቤ ህጉ ባራግ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ፖሊስ ዛሬ በህግ ጥላ ስር ይውላሉ ከተባሉት ትራምፕ ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችለውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር በተጠንቀቅ ላይ መሆኑ አስታውቋል፡፡
በዚህም በኒውዮርክ፣ ዋሽንግተን ዲሲ እና ሎስ አንጀለስ ያለው የፖሊስ ኃይሎች ስምሪት መጠናከሩ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ትራምፕ በቁጥጥር ስር የሚውሉ ከሆነ የማንሃታን አቃቤ ህግ ከአንዲት የወሲብ ፊልም ተዋናይት ጋር የነበራቸውን ግንኙነትና ተዋናይዋን ዝም ለማስባል ገንዘብ ከፍለዋታል የሚል ክስ ሊመሰርት ይችላል ተብሏል፡፡
ትራምፕ በተባለው የወንጀል ድርጊት የሚከሰሱ ከሆነ በአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ታሪክ በእንዲዘህ አይነት ቅሌት የተከሰሱ የመጀመሪያው መሪ መሆናቸው ነው፡፡
አሁን ላይ የትራምፕ ጉዳይ ሊታይ ይችላል በተባለበት የማንሃታን ፍርድ ቤት አከባቢ ትላንት የብረት ማገጃዎች የተተከሉ ሲሆን በትራምፕ ላይ ክስ መመስረቱ አይቀሬ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
የአሜሪካ ሚዲያዎች በስፋት እንዳስቀመጡት ግምት ከሆነ ፍርድ ቤቱ በትራምፕ ክስ ሊመሰርት፣ የጣት አሻራ እንዲሰጡ ሊደርግ እና ፎቶግራፍ ሊያነሳቸው ይችላል፡፡
ትራምፕ ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው ጋር በተያያዘ የሚፈጠር አለመረጋጋት እንዳይኖር ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በተለይም በኒውዮርኩ የትራምፕ ታዎር አቅራቢያ ከወትሮ በተለየ በርካታ ፖሊሶች እንዳሉም ነው የተገለጸው፡፡
የሲቪል ልብስ የሚለብሱ መርማሪዎችን ጨምሮ ሁሉም የኒውዮርክ ፖሊስ ክፍል አባላት የደንብ ልብሳቸውን ለብሰው በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ትእዛዝ እንደተሰታቸውም ነው የተነገረው፡፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኒውዮርክ ፖሊስና ኤፍቢአይ የጋራ ጸረ ሽብር ኃይል የቀድሞና የወቅቱን ፕሬዝዳንት የመጠበቅ ተልዕኮ ካለው የአሜሪካ ሚስጥራዊ አግልግሎት (US Secret Service ) ጋር ትራምፕን ማሰር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መምከራቸው ተስምቷል፡፡
በዋሽንግተን የሚገኘው የካፒቶል ፖሊስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጅ ይችላል ተብሏል፡፡