“በመንግስት ውስጥ ያለን ስውር መንግስት ካላጠፋነው ያጠፋናል” - ትራምፕ
በ2024ቱ ምርጫ ዳግም አሜሪካን ለመምራት የሚፎካከሩት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ የምርጫ ቅስቀሳቸውን አድርገዋል
ትራምፕ በቴክሳስ ዋኮ ባደረጉት ቅስቀሳ፥ የባይደን አስተዳደር ዋይትሃውስ ዳግም እንዳልገባ የሀሰት ክስ እያቀነባበረብኝ ነው ብለዋል
አሜሪካን በድጋሚ በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የሚወዳደሩት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ የምርጫ ቅሰቀሳቸውን አደርገዋል።
- ትራምፕ፥ የባይደን አስተዳደር በዩክሬን ምድር 3ኛውን የአለም ጦርነት ሊያስጀምር ነው ሲሉ ወቀሱ
- ዶናልድ ትራምፕ በ2024 ምርጫ ዳግም ለፕሬዝዳንትነት ሊወዳደሩ ነው
ዶናልድ ትራምፕ በቴክሳስ ዋኮ ባደረጉት ቅስቀሳ፥ የተጀመረባቸው የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት “ፖለቲካዊ” ጫና መሆኑን ተናግረዋል።
ትራምፕ በሺዎች ለሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ካስተላለፉት የ2 ስአት ገደማ መልዕክት አብዛኛውን ጊዜ የወሰደው በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ ክስ ሊመሰርቱባቸው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የህግ ባለሙያዎችን የወረፉበት ነው።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት “የባይደን አስተዳደር ዳግም ዋይትሃውስ እንዳልገባ የወንጅል ክሱን ሆን ብሎ አቀነባብሮብኛል”ም ነው ያሉት።
ህግን ለፖለቲካዊ ፍላጎት ማስፈጸሚያ እና የፖለቲካ ተቀናቃኝን ማሳደጃ አድርገዋል ያሉትን የባይደን አስተዳደር፥ ያለምንም ማስረጃ ክስ ለመመስረት እየተጣደፈ ነው ሲሉም ከሰዋል።
ትራምፕ ከ2016ቱ ምርጫ አስቀድሞ ከአንዲት ተዋናይት ጋር የነበራቸውን ግንኙነትን ለመደበቅ ገንዘብ ከፍለዋል በሚል በማንሃተን አቃቤህግ ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን ሊታሰሩ እንደሚችሉ ተገልጿል።
የጆርጂያ አቃቤህግም ከ2020ው ምርጫ ጋር በተያያዘ የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል በሚል ፍርድ ቤት ሊያቆማቸው ነው ተብሏል።
የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባለፈው ሳምንት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ “ልታሰር እችላለሁ” የሚል መልዕክት በመለጠፍም ደጋፊዎቻቸን ለአመጽ ዝግጁ እንዲሆኑ ማዘዛቸውን ነው ሬውተርስ ያስታወሰው።
ይህ ንግግራቸው በሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ጭምር ተቃውሞ ያስተናገደ በመሆኑ፥ በትናንቱ ንግግራቸው አቃቤ ህጎቹን ከማብጠልጠል በዘለለ ለአመጽ ተዘጋጁ የሚል መልዕክት አላስተላለፉም ተብሏል።
የአሜሪካ ኢኮኖሚ መውደቅ እና የስራ አጥ ሰዎች ቁጥር መጨመርን በቅስቀሳቸው ያነሱት ትራምፕ፥ “በመንግስት ውስጥ ያለ ስውር መንግስትን ካላጠፋነው ያጠፋናል” ብለዋል።
የሪፐብሊካን ተቀናቃኛቸውን ሮን ደሳንቲስን ጨምሮ የአሜሪካ ጠላቶች ናቸው ያሏቸውን ፖለቲከኞችም ያለምንም ማስረጃ መወረፋቸውንም ቀጥለውበታል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።