የትራምፕ የዩትዩብ አካውንት ከሁለት አመት በኋላ ተከፈተ
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከወራት በፊት ዳግም በተከፈተላቸው የፌስቡክ ገጻቸው ላይም መልዕክት ማጋራት ጀምረዋል
ዶናልድ ትራምፕ በ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚፎካከሩ መግለጻቸው ይታወሳል
ዩትዩብ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አካውንትን ዳግም መክፈቱን አስታወቀ።
የቪዲዮ ማጋሪያው ዩትዩብ ከሁለት አመት በፊት ነበር ከካፒቶል ሂል ነውጥ ጋር በተያያዘ የትራምፕን የዩትዩብ አድራሻ የዘጋው።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት የዩትዩብ አድራሻ በጥር ወር 2021 የተዘጋው ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች እየተጋሩበት ነው በሚል ነበር።
አሁን ላይ ግን ትራምፕ ለ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመፎካከር ስለወሰኑና የመራጮችን መረጃ የማግኘት መብት ላለመጋፋት ከሁለት አመት በላይ የተዘጋው አድራሻቸው ተከፍቷል፤ አዳዲስ ቪዲዮዎችንም መጫን ይችላሉ ብሏል የአልፋቤት እህት ኩባንያው ዩትዩብ።
የትራምፕ አካውንት በቀጣይም የጥላቻ መልዕክቶች ማሰራጫ እንዳይሆን ክትትል እንደሚደረግም ነው ያስታወቀው ኩባንያው።
ፌስቡክና ኢንስታግራምን የሚያስተዳድረው ሜታም ሆነ ትዊተር ለሁለት አመት የዘጓቸውን የዶናልድ ትራምፕ አካውንቶች በቅርቡ መክፈታቸው ይታወሳል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በትናንትናው እለትም ከእገዳው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በፌስቡክ ገጻቸው “ተመልሻለሁ” በሚል ርዕስ የ2016 የምርጫ ቅስቀሳ ቪዲዮ አጋርተዋል።
በትዊተር ገጻቸው ግን እስካሁን ምንም አይነት መረጃ አላጋሩም።
ትራምፕ ደጋፊዎቻቸው የምርጫውን ውጤት አንቀበልም ብለው ባስነሱት ነውጥ ምክንያት ከዋና ዋና ማህበራዊ ሚዲያዎች ሲታገዱ የራሳቸውን “ትሩዝ ሶሻል” የተሰኘ ማህበራዊ ትስስር ገጽ መክፈታቸው ይታወሳል።
በርካታ ተከታይ ያላቸው ግን በፌስቡክ፣ ትዊተር እና ኢንስታግራም በመሆኑ እነዚህን ገጾች ለቀጣዩ ምርጫ ቅስቀሳቸው በስፋት እንደሚጠቀሙባቸው ይጠበቃል።
በዩትዩብ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ተከታይ (ሰብስክራይበር) ያላቸው ዶናልድ ትራምፕ፥ በትዊተር 87 ነጥብ4 ሚሊየን፣ በፌስቡክ 34 ሚሊየን እንዲሁም በኢንስታግራም 23 ሚሊየን ተከታዮችን ማፍራት መቻላቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል።