ትራምፕ፥ የባይደን አስተዳደር በዩክሬን ምድር 3ኛውን የአለም ጦርነት ሊያስጀምር ነው ሲሉ ወቀሱ
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በ2024 ፕሬዝዳንት ሆኜ ከተመረጥኩ ፑቲን እና ዜለንስኪ ፊት ለፊት እንዲነጋገሩ አደርጋለሁ ብለዋል
ሩሲያም ትናንት በኬቭ ድንገተኛ ጉብኝት ላደረጉት ባይደን ምላሽ ሰጥታለች
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጆ ባይደን የባይደን አስተዳደር በዩክሬን ጦርነት የያዘውን አቋም አጣጣሉ።
ትራምፕ “ትሩዝ ሶሻል” በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት፥ “የባይደን አስተዳደር ሆን ብሎም ሆነ ባለማወቅ በዩክሬን እያደረገው ያለው ተሳትፎ ሶስተኛውን የአለም ጦርነት የሚያስጀምር ነው” ብለዋል።
በ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚሳተፉ ያረጋገጡት ትራምፕ ከዚህ ቀደምም በይፋ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ እንደነበርም ነው የሩሲያው ታስ ያስነበበው።
- ቻይና በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከሞስኮ ጋር ከወገነች 3ኛው የዓለም ጦርነት ይነሳል ሲሉ ዘለንስኪ አስጠነቀቁ
- አሜሪካ በ2025 ከቻይና ጋር ጦርነት ውስጥ ልትገባ ትችላለች - የአሜሪካ ጀነራል
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በ2016 ወደ ስልጣን ሲመጡ ከሩሲያ ጋር የነበራቸው ግንኙነትና የሞስኮ የምርጫ ጣልቃገብነት ሲያስከስሳቸው መቆየቱ ይታወሳል።
ትራምፕ በትናንትናው እለት በፍሎሪዳ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉም፥ “እኔ በስልጣን ላይ ብሆን (ፕሬዝዳንት) ፑቲን ወደ ዩክሬን በፍጹም አይገባም ነበር፤ ከፑቲን ጋር ጥሩ ወዳጅነት አለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
በ2018 ከአሜሪካ ጋዜጠኞች ለተነሳላቸው “የኛን የደህንነት ሹሞች ነው ወይስ ፑቲንን ነው የሚያምኑት?” ጥያቄ የሰጡት ምላሽ አሁንም ድረስ ትክክል መሆኑንም አንስተዋል፤ ትራምፕ በወቅቱ የመለሱት በአጭሩ “ፑቲንን አምናለሁ” የሚል ነበር።
በትናንቱ የፍሎሪዳው ቅስቀሳችውም በቀጣዩ አመት ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ቀዳሚው ስራቸው ፑቲን እና ዜለንስኪን ፊት ለፊት አገናኝቶ ማደራደር እንደሆነ መናገራቸውን ኤ ቢ ሲ ኒውስ ዘግቧል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዋነኛ የቅስቀሳ ርዕስ ያደርጉታል ተብሎ የሚጠበቀው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከሶስት ቀናት በኋላ አንደኛ አመቱን ይይዛል።
በዚህ ሚሊየኖችን ባፈናቀለ ጦርነት ውስጥ አሜሪካ የዩክሬን ሁነኛ ደጋፊ ሆና ቆይታለች።
ይህንንም በትናንቱ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የኬቭ ድንገተኛ ጉብኝት ማሳየቷን ነው ታስ የሚገልጸው።
ዋይትሃውስ ለዩክሬን የ450 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍ ይፋ ማድረጉና የጦር መሳሪያ የማስታጠቁ ጉዳይ ተጠናክሮ መቀጠሉ ዩክሬንን የሃያላኑ መፋጠጫና የሶስተኛው የአለም ጦርነት ማስጀመሪያ እንዳያደርጋት ስጋቱ ከፍ እያለ ነው።
ለኬቭ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከ27 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ያደረገችው ዋሽንግተን፥ ቻይና ከሩሲያ ጎን ከተሰለፈች ጦርነቱ ይበልጥ መልኩን እንደሚቀይርም አሳስባለች።
ሞስኮ ግን የጦርነቱ መነሻ የምዕራባውያን በኔቶ በኩል የመስፋፋት ፍላጎት ነው፤ ለኬቭ ጥይት በማቀበልም ጦርነቱ እንዲራዘም እያደረጉ ነው በሚል ትከሳለች።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዛሬው እለት ለባይደን የኬቭ ጉብኝት በሰጡት ምላሽም፥ ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር ከተፈራረመችው የኒዩክሌር ስምምነት መውጣቷን ይፋ አድርገዋል።