ከአስር አሜሪካውያን አራቱ ከዘንድሮው ምርጫ በኋላ ግጭት ሊፈጠር እንደሚችል ያምናሉ ተባለ
አሜሪካውያን መራጮች ከምርጫው በኋላ ብጥብጥ እና ውጤቱን ለመቀልበስ የሚደረግ ጥረት እንደሚያሳስባቸው ተነግሯል
አሜሪካ ወደ ቀድሞ የአመጻ ፖለቲካ እና ብጥብጥ ትመለስ ይሆን የሚለው ስጋት በርካታ አሜሪካውያን የሚጋሩት ሀሳብ ነው
አሜሪካውያን ከድህረ ምርጫ በኋላ ምን ሊከሰት ይችላል በሚል ጭንቀት ውስጥ ወደ 2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እየተቃረቡ ነው፡፡
ይህ ጭንቀታቸው የድህረ ምርጫ ብጥብጥ እና ውጤቱን ለመቀልበስ የሚደረጉ ሙከራዎች የዴሞክራሲ ቁንጮ በተባለው የአሜሪካ ፖለቲካ ስርአት ላይ ተጽዕኖውን ሊያሳድር ይችላል ከሚል የመነጨ እንደሆነ ኤፒ ዘግቧል፡፡
ከአራት አመት በፊት የ2020ውን ምርጫ ውጤት አልቀበልም ያሉት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎቻቸው ወደ ካፒቶል ሂል ሄደው ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ በይፋ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ ጊዜ በኋላ ደግሞ በዘንድሮው ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በሪፐብሊካኑ ዕጩ ትራምፕ ላይ ሁለት ጊዜ የግድያ ሙከራዎች እንደተቃጣባቸው አይዘነጋም፡፡
ይህንን ተከትሎም አሜሪካ ወደ ቀድሞ የአመጻ ፖለቲካ እና ብጥብጥ ትመለስ ይሆን የሚለው ስጋት በብዙ አሜሪካውያን መራጮች አዕምሮ ውስጥ የሚመላለስ ሀሳብ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
የአሶሼትድ ፕረስ የህዝብ ጉዳዮች የምርምር ማዕከል ባሰባሰበው የህዝብ ድምጽ ከአስር አሜሪካውያን መራጮች መካከል አራቱ ከዘንድሮው ምርጫ በኋላ ብጥብጥ እና የምርጫውን ውጤት ለመቀልበስ የሚደረጉ ጥረቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ስጋት እንዳላቸው ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ ከ3ቱ መራጮች መካከል አንዱ የአካባቢ ወይም የግዛት የምርጫ አስፈፃሚዎች ውጤቱ እንዳይጠናቀቅ ለማስቆም ፣ በምርጫው ጣልቃ ለመግባት ሙከራ ሊያደርጉ እንደሚችል እምነት አላቸው፡፡
ከዚህ ውስጥ ምርጫው በሰላም እንደሚጠናቀቅ እና ጤናማ የስልጣን ሽግግር ሂደት ሊኖር እንደሚችል እምነት ያላቸው አንድ ሶስተኛ ብቻ መራጮች ናቸው፡፡
ከአራት አመት በፊት የተሸነፉት በተጭበረበረ ድምጽ እንደሆነ አሁንም መናገራቸውን የቀጠሉት ዶናልድ ትራምፕ በዚህኛው ዙር ምርጫም ሊሸነፉ የሚችሉት በማጭበርበር ብቻ ሊሆን እንደሚችል መተንበያቸውን አላቆሙም፡፡
የኤፒ የጥናት ማዕከል ባሰባሰበው ደምጽ በርካታ መራጮች ትራምፕ የሚሸነፉ ከሆነ ውጤቱን አምኖ ለመቀበል የሚችገሩ ሰው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በዴሞክራት እና ሪፐብሊካን መራጮች ዘንድ ያለው ሀሳብ የተለያየ ነው፡፡
ከሪፐብሊካን መራጮች መካከል ሁለት 3ኛ ያህሉ ትራምፕ ውጤቱን እንደሚቀበሉ ያስባሉ፤ በአንጻሩ ከ10 ዲሞክራቶች አንዱ ብቻ የምርጫውን ውጤት ሊቀበሉ እንደሚችል ተናግሯል፡፡
ተቀናቃኛቸው ካማላ ሃሪስን በተመለከተ ከ10 ሰዎች መካከል ስምንቱ የምርጫ ውጤቱን በሰላማዊ መንገድ ሊቀበሉ እንደሚችሉ እምነት አላቸው፡፡
ነገር ግን በሁሉቱም መንገድ የዘንድሮው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የአሜሪካ የዴሞክራሲ ጉዞን የሚወስን ሊሆን እንደሚችል ከ50 በመቶ በላይ መራጮች ያስባሉ፡፡