ትራምፕ በቀረቡባቸው 34 ክሶች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ስንት አመት ይታሰራሉ?
ትራምኘ ከሁለት ሴቶች ጋር የነበራቸውን የወሲብ ግንኙነት ለመደበቅ ክፍያ ከመፈጸም ጋር የተያያዘ ክስም ቀርበውባቸዋል
የ2014ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ የኒውዮርኩን ክስ “የምርጫ ጣልቃገብነት” ነው ብለውታል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በወንጀል ተጠርጥረው ትናንት በኒውዮርክ በሚገኘው የማንሃተን ፍርድ ቤት ቀርበው ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ትራምፕ የ2016ቱን ምርጫ በስኬት ለማጠናቀቅ ፈጽመዋቸዋል የተባሉ 34 ወንጀሎችም ቀርበዋል።
ከምርጫው በፊት ከሁለት ሴቶች ጋር ፈጸሙት የተባለውን የወሲብ ግንኙነት ለመሸፈን ለሴቶቹ በድምሩ 280 ሺህ የአሜሪካ ዶላር መክፈላቸው በአቃቤ ህጎች ቀርቧል።
ከቢዝነስ ጋር የተገናኙ የሰነድ ማጭበርበር ክሶችም ቀርበዋባቸዋል።
የቢዝነስ ሰነዶችን ማሳሳት በኒውዮርክ ከአንድ አመት በማይበልጥ እስራት ያስቀጣል።
የማንሃተን ፍርድ ቤት ለታህሳስ 4 2023 ቀጠሮ ይዟል። የክስ ሂደቱ ከአመት በላይ የሚወስድ መሆኑን የሚጠቅሱ የህግ ባለሙያዎች ትራምፕ በ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያግዳቸው ነገር እንደማይኖር ይገልጻሉ።
የሰነድ ማጭበርበሩ የምርጫ ህጉን በተጻረረ መልኩ ያልተገባ ውጤትን ለማግኘት በማለም ከተካሄደ ደግሞ የወንጀል ድርጊቱ እስከ አራት አመት እስራትን ሊያስከትል ይችላል።
በፍርድ ቤቱም ሆነ ከፍርድ ቤት ከወጡ በኋላ ምንም ያልተናገሩት ትራምፕ ወደ ፍሎሪዳ በማቅናት ለቤተሰቦቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ፥ የቀረበባቸው ክስ የምርጫ ጣልቃገብነት መሆኑን ገልጸዋል።
“በአሜሪካ እንዲህ አይነት ነገር ይፈጸማል ብዬ አስቤ አላውቅም” ያሉት ዶናልድ ትራምፕ፥ “የሰራውት ብቸኛ ወንጀል ሀገራችን ሊያጠፏት ከሚሰሩ ወገኖች መታገሌ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ትራምፕ በጆርጂያም የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሽንፈታቸውን ባለመቀበል ፈጽመውታል የተባለ የወንጀል ድርጊት ክስ ይጠብቃቸዋል።
የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴርም እንዲሁ ከሶስት አመት በፊት ከተካሄደው ምርጫ ጋር በተገናኘ የወንጀል ምርመራ እያደረገባቸው ይገኛል።
“በምርጫ ካርድ እንደማያሸንፉኝ ሲያውቁ በህግ ሊረቱኝ እየሞከሩ ነው” ያሉት አወዛጋቢው ሰው ግን ክሶቹን መሰረተ ቢስ መሆናቸውን ምሽቱን በፍሎሪዳ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።