ትራምፕ የፊታችን ማክሰኞ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በካቴና አይታሰሩም - ጠበቃቸው
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሰኞ በግል አውሮፕላናቸው ወደ ኒውዮርክ በማቅናት እጃቸውን ይሰጣሉ ተብሏል
ዶናልድ ትራምፕ በወሲብ ቅሌት ፍርድ ቤት የሚቀርቡ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፊታችን ማክሰኞ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ተገልጿል።
ትራምፕ በፍሎሪዳ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በግል አውሮፕላናቸው ሰኞ ወደ ኒውዮርክ እንደሚያቀኑም ሬውተርስ ዘግቧል።
በዚህ በአይነቱ ልዩ በሆነው ክስተት ከመቶ በላይ የአሜሪካ የኢደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) እና ልዩ የደህንነት ባለሙያዎች እንደሚሳተፉም ነው የተነገረው።
ጉዟቸውም ሆነ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ደህንነታቸው እንዲጠበቅም እጃቸውን ለፌደራል የጸጥታ ሃይሎች ይሰጣሉ ተብሏል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንትይ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እጃቸው በካቴና አይታሰርም ያሉት ጠበቃቸው ጆሴፍ ታኮፒና፥ ስለክሱ ዝርዝር ባይናገሩም በ2016 ፈጸሙት ከተባለ የወሲብ ቅሌት ጋር እንደሚያያዝ ተገልጿል።
ትራምፕ ስቶርሚ ዳኔልስ ከተባለች ሴት ጋር የፈጸሙትን ግንኙነት ለመሸፋፈን 130 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ክፍያ መፈጸማቸውን ክሱ ያሳያል የሚለው ሲ ቢ ኤስ ኒውስ ዝርዝሩ በማንሃተን ፍርድ ቤት ማክሰኞ ሲቀርቡ ይታወቃል ብሏል።
አሶሼትድ ፕረስ ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ ከ30 በላይ ከቢዝነስ ጋር የተያያዙ ክሶች ሊቀርብባቸ እንደሚችል ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሰኞ እለት በትራምፕ ታወር አዳራቸውን አድርገው ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው በፊት ተቃውሞ እንዳይቀሰቀስ ተሰግቷል።
ትራምፕ “ከታሰርኩ ትርምስ ይፈጠራል” በሚል ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎም በኒዮርክ የጸጥታ ሁኔታውን ለመጠበቅ ሰፊ እንቅስቃሴ መደረጉ ነው እየተዘገበ ያለው።
በትናንትናው እለት የ2024 ምርጫ ቅስቀሳ እና የገቢ ማሰባሰቢያ ያደረጉት ትራምፕ፥ ከክሱ ጋር በተያያዘ “ምንም የሚያስፈራኝ የለም” ብለዋል።
እንደከዚህ ቀደሙም የብጥብጥ ጥሪ አለማቅረባቸውን ነው ሬውተርስ የዘገበው።
ዋይትሃውስ ዳግም ለመግባት ፉክክሩን የተቀላቀሉት አወዛጋቢ ሰው የሚቀርብባቸው ክስ በአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ታሪክ የመጀመሪያው መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በ2024ቱ ምርጫ ላይ ጥቁር ጠባሳ እንደሚጥልባቸው ይጠበቃል።