በአፍጋኒስታን ጥለናቸው የወጣነውን 70 ሺህ ተሽከርካሪዎች ማስመለስ አለብን - ትራምፕ
ታሊባን ከ7 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ የአሜሪካ የጦር መሳሪያዎችን እየቸበቸበ "የአለማችን ቀዳሚው የጦር መሳሪያ ሻጭ ሁኗል" ሲሉም ተናግረዋል

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የባይደን አስተዳደር የአሜሪካ ወታደሮችን ከካቡል ያስወጣበትን መንገድ ተችተዋል
አሜሪካ ከአራት አመት በፊት ከአፍጋኒስታን ጥላቸው የወጣቻቸውን የጦር መሳሪያዎቿን ማስመለስ እንደምትፈልግ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ትናንት ምሽት የመጀመሪያ የካቢኔ ስብሰባቸውን ሲያደርጉ አስተዳደራቸው የአሜሪካ ጦርን ከአፍጋኒስታን የማስወጣቱን ሂደት በመሩ ወታደራዊ አዛዦች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
ትራምፕ በምላሻቸው የባይደን አስተዳደር ከአራት አመት በፊት የአሜሪካ ወታደሮችን ከካቡል ያስወጣበትን መንገድ ተችተዋል።
በፓርዋን ግዛት የሚገኘውን የባግራም የአየር ማዛዣ ጣቢያ መልቀቅ አልነበረብንም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ ቻይና የአሜሪካን የጦር ማዘዣ መቆጣጠሯን ተናግረዋል። ቤጂንግ ግን ይህን ወቀሳ አልተቀበለችውም።
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው የጀመሩትንና በባይደን አስተዳደር የተፈጸመውን ከአፍጋኒስታን የመውጣት ሂደት ባብራሩበት ንግግራቸው ትኩረት የሰጡት ያልተመለሱ የጦር መሳሪያዎችን ጉዳይ ነው።
አሜሪካ ከካቡል ስትወጣ ከ7 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ቦምቦችና ሚሳኤሎችን ጨምሮ የተለያየ አይነት የጦር መሳሪያዎች፣ አውሮፕላኖች፣ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችና የኮሙዩኒኬሽን መሳሪያዎች በዚያው ቀርተዋልም ነው ያሉት።
ታሊባን የአሜሪካ የጦር መሳሪያዎች የራሱ አስመስሎ ለትርኢት ከማቅረብ አልፎ ለሽያጭ በማቅረብ "የአለማችን ቀዳሚው የጦር መሳሪያ ሻጭ ሆኗል" ሲሉም አብራርተዋል።
"ታምናላችሁ? 770 ሺህ ጠምጃዎችን እየሸጡ ነው፤ 70 ሺህ ጥይት የማይበሳቸው ተሽከርካሪዎችን ትተንላቸው ነው የወጣነው፤ እንደኔ እምነት ሁሉንም መሳሪያዎቻችን ማስመለስ አለብን" ብለዋል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴርን ዋቢ አድርጎ ፎሬን ፖሊሲ እንዳስነበበው አሜሪካ ከፈረንጆቹ 2005 እስከ 2021 ድረስ ለአፍጋኒስታን ብሄራዊ ጦር እና ሌሎች የጸጥታ አካላት ከ18.6 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎች ሰጥታለች።
ታሊባን ዳግም ስልጣን ከያዘ በኋላም ዋሽንግተን ለካቡል የ21 ቢሊየን ዶላር ሰብአዊ ድጋፍ አድርጋለች።
ይሁን እንጂ ታሊባን የአፍጋኒስታን የፖለቲካ ስርአትን እንዲያሻሽል ከአሜሪካ የሚቀርብለትን ጥያቄ በሚገባ እየመለሰ አይደለም ይላል የፎሬን ፖሊሲ መጽሄት።
የትራምፕ አስተዳደርም ቡድኑ መሰረታዊ ርዕዮተ አለማዊ እሳቤውን እንደማይለውጥ በማመን ከ7 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎች ይመለሱልን የሚል ጠንካራ አቋምን በማንጸባረቅ ጫና መፍጠርን መርጧል።
ታሊባን በበኩሉ አለማቀፋዊ ተቀባይነት እና በዋሽንግተን እንዳይንቀሳቀስ የታገደውን የአፍጋኒስታን ማዕከላዊ ባንክ ሃብት ለማግኘት ከትራምፕ አስተዳደር ጋር የተሻለ ግንኙነት መመስረት ይፈልጋል ተብሏል።
ይሁን እንጂ የትራምፕን የጦር መሳሪያዎቻችን መልሱ ጥያቄ ይቀበለዋል ተብሎ አይጠበቅም። በአፍጋኒስታን ድንበር የሚንቀሳቀሰውን "አይኤስ ኮርሳን" ለመዋጋት የዋሽንግተን የጦር መሳሪያዎች ወሳኝ ናቸው የሚል ምክንያትም ሊያቀርብ ይችላል።
ዘገባው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለታሊባን ያቀረቡት ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው በጠመንጃ ብቻ ከሆነ ሌላ አውዳሚ ጦርነት መጀመር ይኖርባቸዋል፤ ይህ ግን የሚሆን አይመስልም ይላል። ካቡል የሁለቱን ኒዩክሌር የታጠቁ ሀገራት ወረራ መቋቋሟንም በማውሳት።
የያኔዋ ሶቪየት ህብረት በ1970ዎቹ፤ አሜሪካ ደግሞ ከመስከረም 11ዱ ጥቃት በኋላ ወደ አፍጋኒስታን ቢዘልቁም እንዳሰቡት አልሆነላቸውም። ዋሽንግተን ከሁለት አስርት አመታት በኋላ ያለምንም ድል ጦሯን ከካቡል ማስወጣቷ ይታወሳል።