አሜሪካ በኢምባሲዎቿ ያሏትን ሰራተኞች እና ዲፕሎማቶች ልትቀንስ ነው
በተለያዩ ሀገራት ያሉ የአሜሪካ ኢምባሲዎች ሰረተኞቻቸውን እንዲቀንሱ ታዘዋል ተብሏል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/14/258-174333-p4tlfhmhv5iz7eiaxzthxxleme_700x400.jpg)
የሰራተኛ ቅነሳው ኢምባሲዎቹ በሚገኙባቸው ሀገራት ያሉ ዜጎችንም እንደሚመለከት ተገልጿል
አሜሪካ በኢምባሲዎቿ ያሏትን ሰራተኞች እና ዲፕሎማቶች ልትቀንስ ነው።
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ በተለይም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የሰራተኛንቅነሳ ላይ ትገኛለች።
አሜሪካ ትቅደም በሚል የሚታወቁት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በመላው ዓለም ባሉ የአሜሪካ ኢምባሲዎች ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን ሊቀንሱ ነው ተብሏል።
ሮይተርስ እንደዘገበው ከሆነ የሰራተኛ ቅነሳው ከአሜሪካዊያን ባለፈ ኢምባሲዎቹ በሚገኙባቸው ያሉ ሀገራት ዜጎችንንም ይመለከታል።
ኢምባሲዎች እስከ 10 በመቶ ሰራተኞቻቸውን እንዲቀንሱ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በኩል ተነግሯቸዋልም ተብሏል።
አሜሪካ በመላው ዓለም ባሉ ኢምባሲዎቿ ውስጥ ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩ ሰራተኞቿን ለመቀነስ ያቀደችው ወጪ ቅነሳ በሚል ምክንያት እንደሆነም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን በመጡበት ዕለት ከአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ውጪ ሌሎች የውጭ እርዳታዎችን ለሦስት ወራት ማራዘማቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ እገዳውን ያስተላለፉት እርዳታዎቹ የአሜሪካንን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ስለመተግበራቸው እርግጠኛ መሆን ስለፈለጉ እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም በአሜሪካ የፌደራል መንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ስራ እንዲለቁም አድርገዋል።
በዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ ምክንያትም ከ70 ሺህ በላይ አሜሪካዊያን የመንግስት ሰራተኞች ስራቸውን ለቀዋል ተብሏል።