ትራምፕ ስራ ለሚለቁ የፌደራል ሰራተኞች የስምንት ወር ደመወዝ ሊከፍሉ ነው
ከ2 ሚሊየን የፌደራል ሰራተኞች 10 በመቶው የቀረበውን የስራ ማሰናበቻ ይቀበሉታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር አስታውቋል
ሰራተኞቹ ውሳኔያቸውን እስከ ቀጣዩ ሳምንት እንዲያሳውቁ የኢሜል መልዕክት ደርሷቸዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስራ ለመልቀቅ ለሚስማሙ የፌደራል ሰራተኞች የስምንት ወር ደመወዛቸውን እንደሚከፍሉ አስታወቁ።
ለሚሊየኖች የፌደራል ሰራተኞች የተላከው የኢሜል መልዕክት ሰራተኞች እስከ የካቲት 6 2025 ድረስ ውሳኔያቸውን እንዲያሳውቁ ይጠይቃል።
ስራቸውን ለቀው ዳግም ወደ ቢሯቸው መመለስ የማይሹ ሰራተኞች የስምንት ወር ደመወዛቸው እንደ ማሰናበቻ ሆኖ ይከፈላቸዋል ይላል መልዕክቱ።
የትራምፕ አስተዳደር ከአጠቃላይ የፌደራል ሰራተኞች (ከ2 ሚሊየን በላይ) ውስጥ 200 ሺህ የሚጠጉት የቀረበውን የስራ ማሰናበቻ ፓኬጅ እንደሚቀበሉት ይጠብቃል ብሏል የሲቢኤስ ዘገባ።
ይህም የአሜሪካ መንግስትን ከ100 ቢሊየን ዶላር በላይ እንዲያድን ያግዘዋል ብለዋል ስማቸው ያልተጠቀሰ ከፍተኛ ባለስልጣን።
ስራቸውን መልቀቅ የሚፈልጉ ሰራተኞች ለተላከላቸው ኢሜል "መልቀቅ እፈልጋለሁ" የሚል አጭር መልዕክት መመለስ በቂያቸው ነው። በዚህም እስከ መስከረም 30 2025 ድረስ ወርሃዊ ደመወዛቸው ተሰልቶ እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።
የፖስታ ቤት ሰራተኞች፣ የአሜሪካ ጦር አባላት፣ የስደተኞች ጉዳይ አመራሮች እና የተወሰኑ የብሄራዊ ደህንነት ሰራተኞች ከትራምፕ አስተዳደር ለፌደራል ሰራተኞች የተላከው ኢሜል አልደረሳቸውም።
በአወዛጋቢ ውሳኔያቸው የሚታወቁት ዶናልድ ትራምፕ የፌደራል መስሪያቤቶችን እና ሰራተኞችን ቁጥር መቀነስ እንደሚፈልጉ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ትራምፕ "መንግስታቸውን ለመቆጣጠር ለ2 ሚሊየን የፌደራሉ መንግሥት ሰራተኞች ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አምነዋል" ይላሉ የዋይትሃውስ የፖሊሲ ምክትል ኃላፊ ስቴፈን ሚለር ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ።
የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ኤለን መስክ እና ቪቬክ ራማስዋማይንም ይህንኑ ስራ እንዲያግዟቸው መሾማቸውም የሰጡትን ትኩረት ማሳያ ተደርጎ ይነሳል።
በትናንትናው እለት ለፌደራል ሰራተኞች የተላከው የኢሜል መልዕክት መስክ በ2022 የያኔውን ትዊተር (የአሁኑ ኤክስ) ከገዛ በኋላ ለሰራተኞቹ ከላከው መልዕክት ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ነው ተብሏል።
እስከ ቀጣይ ሳምንት ከስራቸው ለመልቀቅ ፍላጎታቸውን የማያሳዩ የፌደራል ሰራተኞች በቀጣይ ያለምንም የስራ ማሰናበቻ ጥቅማጥቅም ሊባረሩ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው።
ትራምፕ በኮቪድ ምክንያት ስራቸውን በቤታቸው ያደረጉ ሰራተኞች ወደ ቢሯቸው ተመልሰው በሳምንት ለአምስት ቀናት እንዲሰሩ ማሳሰባቸው ይታወሳል።