ትራምፕ "የወንበዴ" ቡድን አባላት ናቸው ያሏቸውን ከ200 በላይ ቬንዙዌላውያን ከአሜሪካ አባረሩ
ፕሬዝዳንቱ በጦርነት ጊዜ የሚታወጅ ህግን ተጠቅመው ስደተኞችን በገፍ እንዳያባርሩ በአሜሪካ የፌደራል ዳኛ የተላለፈባቸውን እገዳ ጥሰው ነው እርምጃውን የወሰዱት

ኤልሳቫዶር 238 "ትሬን ደ አራጉዋ" የተሰኘ የወንበዴ ቡድን አባላትን 40 ሺህ እስረኞችን በሚይዝ ማረሚያ ቤቷ ውስጥ እንደምታስር አስታውቃለች
የትራምፕ አስተዳደር የወንበዴ ቡድን አባላት ናቸው በሚል የጠረጠራቸውን ከ200 በላይ ቬንዙዌላውያን ከአሜሪካ አባረረ።
የኤልሳቫዶር ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬሌ 238 "ትሬን ደ አራጉዋ" የተሰኘ የወንበዴ ቡድን አባላትን ያሳፈረው የአሜሪካ አውሮፕላን ሳን ሳልቫዶር መድረሱን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
23 "ኤምኤስ - 13" የተሰኘ አለማቀፍ የወሮበላ ቡድን አባላትም በማዕከላዊ አሜሪካዋ ሀገር መድረሳቸውን ነው የጠቆሙት።
የቬንዙዌላው የወንበዴ ቡድን "ትቴን ደ አራጉዋ" ዜጎችን አፍኖ በመውሰድ፣ በዘረፋ እና በግድያ የተሰማራ መሆኑ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጦርነት ጊዜ የሚታወጅ ህግን ተጠቅመው ስደተኞችን በገፍ እንዳያባርሩ በአሜሪካ የፌደራል ዳኛ ጀምስ ቦስበርግ የተላለፈባቸውን የእገዳ ውሳኔ ጥሰው ነው እርምጃውን የወሰዱት።
የዋይትሃውስ ቃል አቀባይ ካሮሊን ሌቪት ግን "በአንድ ከተማ የሚገኝ አንድ ዳኛ የውጭ ሀገር ስደተኞችን የጫነ አውሮፕላን ከአሜሪካ መሬት እንዳይወጣ መከልከል አይችልም፤ የእገዳ ውሳኔው ህጋዊ አይደለም" በሚል ተከላክለዋል።
ቃል አቀባዩዋ የፌደራል ዳኞች የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በውጭ ጉዳዮች ላይ የሚያሳልፏቸውን ውሳኔዎች የመቀልበስ ስልጣን እንደሌላቸው መናገራቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕም የዳኛውን የእገዳ ውሳኔ ጥሰዋል ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ "ልነግራችሁ የምችለው እነዚህ መጥፎ ሰዎች መሆናቸውን ነው" የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።
ትራምፕ 227 አመት የሆነውንና አሜሪካ ጦርነት ውስጥ ስትገባ የሚታወጅ ህግ የተጠቀሙት የስደተኞች ቁጥር መብዛትና ወንጀሉም መበራከቱ ከጦርነት ጋር ስለሚስተካከል ነው በሚል ነው።
አሜሪካ ይህን ህግ ለመጨረሻ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገችው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጃፓናዊያንን ለማባረር እንደነበር የቢቢሲ ዘገባ አውስቷል።
የ78 አመቱ ፕሬዝዳንት ባለፈው ቅዳሜ የ1798ቱን ህግ ተጠቅመው "ያልተለመደ ጦርነት ከፍተዋል" ያሏቸውን የቬንዙዌላ የወንበዴ ቡድን አባላት ከአሜሪካ እንደሚያባርሩ መናገራቸው ይታወሳል።
የፌደራሉ ዳኛ ጀምስ ቦስበርግ ስደተኞቹን የማባረሩ ሂደት "መለዮ ከማይለብሱ ጋር የሚደረግ ከጦርነት የከፋ ጦርነት ነው በሚል" የትራምፕን ውሳኔ ለ14 ቀናት አግደውት ነበር።
ዳኛው ውሳኔያቸውን ባሳወቁበት ወቅት ቬንዙዌላውያኑን የጫኑ አውሮፕላኖች ወደ ኤልሳቫዶር ጉዞ መጀመራቸውን መስማታቸውን በመጥቀስም አውሮፕላኖቹ ወደ አሜሪካ እንዲመለሱ አዘው ነበር።
በማግስቱ (ትናንት) የኤልሳቫዶር ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬሌ በኤክስ ትስስር ገጻቸው ቬንዙዌላውያኑን የጫኑ አውሮፕላኖች ሳን ሳልቫዶር መግባታቸውን የሚያሳይ ምስልን ሲያጋሩ "ዘግይተዋል" በሚል በዳኛው ላይ ተሳልቀዋል።
ከአሜሪካ ወደ ኤልሳቫዶር የተላኩት የ"ትሬን ደ አራጉዋ" ወንበዴ ቡድን አባላት 40 ሺህ እስረኞችን መያዝ ወደሚችለው የሽብርተኞች ማረሚያ ቤት እንደሚገቡ ፕሬዝዳንት ቡኬሌ አስታውቀዋል።