የኔቶ ኃላፊ ዘለንስኪ ከትራምፕ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማስተካከል እንዳለባቸው አሳሰቡ
ሩቴ ይህን ያሉት ዘለንስኪ ከፕሬዝደንት ትራምፕ ጋር ባለፈው አርብ በኃይትሀውስ ተጋጭተው ግንኙነታቸው መበላሸቱን ተከትሎ ነው

ሩቴ ትራምፕ "ፕሬዝደንት ትራምፕ እስካሁን ለዩክሬን ላደረጉት ማመስገን ይገባል" ብለዋል
የኔቶ ኃላፊ ማርክ ሩቴ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያስተካክሉበትን መንገድ እንዲፈልጉ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።
ሩቴ ይህን ያሉት ዘለንስኪ ከፕሬዝደንት ትራምፕ ጋር ባለፈው አርብ በኃይትሀውስ ተጋጭተው ግንኙነታቸው መበላሸቱን ተከትሎ ነው።
በሁለቱ ፕሬዝደንቶች መካከል የነበረው ፍጥጫ ሶስት አመታት ያስቆጠረው የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት እንዴት ይቁም በሚለው ነጥብ ላይ ጉልህ ልዩነት የታየበት ነው።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ዩክሬን ጦርነቱ ከመቆሙ በፊት ከአሜሪካ የደህንነት ዋስትና እንዲሰጣት የምትፈልግ ሲሆን ትራምፕ ደግሞ ከሩሲያው መሪ ፑቲን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ንግግር በማድረግ ጦርነቱን ለማስቅም ንግግር ጀምረዋል።
ሩቴ "ያልተሳካ"ሲሉ የገለጹት ስብሰባ በኪቭና በዋና ደጋፊዋ አሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ዝቅተኛ ደረጃ አድርሶታል።
" ውድ ቮሎድሚር ከዶናልድ ትራምፕና ከአሜሪካ አስተዳደር ጋር ግንኙነትህን የምታድስበትን መንገድ መፈለግ አለብህ ብዬ ነግሬዋለሁ። ያ ነው ወደፊት የሚያስኬደው" ሲሉ ሩቴ ለቢቢሲ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሩቴ ትራምፕ በ2019 ጃቭሊን ጸረ-ታንክ ሚሳይል ለዩክሬን መስጠታቸውን በማስታወስና የሩሲያን ጥቃት ለመመከት እንደረዳት በማስታወስ "ፕሬዝደንት ትራምፕ እስካሁን ለዩክሬን ላደረጉት ማመስገን ይገባል" ብለዋል።
ሩቴ እንደገለጹት ከሆነ በ2022 አጠቃላይ ጦርነቱ ሲጀመር ዩክሬን ጃቭሊን ሚሳይልን ባትታጠቅ ኖሮ የትም አትደርስም ነበር።
"ትራምፕና አሜሪካ ላደረጉትና እያደረጉ ላሉት ድጋፍ ማመስገን እንደሚገባን ነግሬዋለሁ" ብለዋል ሩቴ። ሁለቱ መሪዎች በተለዋወጧቸው ክሶች ዙሪያ መናገር ያልፈለጉት የኔቶ ኃላፊ አሜሪካ በወታደራዊ ጥምረቱ ላይ ከባድ ኢንቨስትመንት አድርጋለች ብለዋል። ሩቴ ትራምፕ ጥሩ ጓደኛ መሆናቸውን ቢገልጹም ትራምፕ "በሶስተኛ የአለም ጦርነት እየቆመርክ ነው" ሲሉ በዘለንስኪ ላይ ያቀረቡት ክስ እና ትራምፕ ለዘንስኪ የብርቅዬ ማዕድናት ውል ትፈርማለህ ወይም አሜሪካ ከሂደቱ ትወጣለች ሲሉ የተናገሩት ትክክል ስለመሆኑ ተጠይቀው ቀጥተኛ መልስ አልሰጡም።
ሩቴ አሜሪካ በዩክሬን አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ ትፈልጋለች የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ ብታቆም የሚፈጠረውን ክፍተት የኔቶ ጥምረት ይሸፍነው እንደሆነ የተጠየቁት ሩቴ "ከዚህ ጥያቄ ባሻገር እንሂድ። አሜሪካ፣ አውሮፓና ዩክሬን አብረን መቆየታችን ወሳኝ ነው" ሲሉ መልሰዋል።