የትራምፕና የዘሌንስኪን ዱላቀረሽ ክርክር ተከትሎ የዓለም ሀገራት መሪዎች ምን አሉ?
ትራምፕ ዘለንስኪን “አሜሪካን አላከበርክም"ሲሉ፤ ዘለንስኪ ዋይት ኃውስን ጥለው ወጥተዋል

በርካታ የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ክርክሩን ተከትሎ ከዘሌንስኪ ጎን መሆናቸውን እየገለጹ ነው
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ በዋይት ኃውስ ያደረጉት ውይይት ያለ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የበርካታ ሀገራት መሪዎች አስተያየት እየሰጡ ነው።
ዘለንስኪ ወደ ዋይት ኃውስ ያቀኑት በውድ ማእድናት ዙሪያ ከአሜሪካ ጋር ስምምት ለመፈራረም ቢሆን፤ ሁለቱ ውይይት ወደ ክርክር እና የቃላት ግጭት አምርቶ ያለ ምንም ሰምምት ተጠናቋል።
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጋር የጦፈ ክርክር ካደረጉ በኋላ ነው ስምምነቱ የተቋረጠው።
ይህንም ተከትሎ ትራምፕ ዘለንስኪን “አሜሪካን አላከበርክም" ሲሉ፤ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ዋይት ሀውስን ጥለው ወጥተዋል።
የትራምፕና የዘሌንስኪን ዱላቀረሽ ክርክር ተከትሎ የዓለም ሀገራት መሪዎች አስተያየታቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ትራምፕ የዘለንስኪን ክብር በነካ መልኩ የተናገሩትን ንግግር ተከትሎ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ከቮሊድሚር ዘሌንስኪ ጎን መሆናቸውን በመናገር ላይ ይገኛሉ።
ለዘሌንስኪ ድጋቸውን ከገለጹ ሀገራት መካከልም ጀርመን፣ ሰፔን፣ ፈረንሳይ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ አየርላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድስ እንዲሁም የአውሮፓ ፓርላማ፣ የአውሮፓ ኮሚሽን እና የአውሮፓ ካውንስል ይገኙበታል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኤል ማክሮን፣ ለዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
“ከሶስት ዓመት በፊት ዩክሬንን ደግፈን ሩሲያ ላይ ማዕቀብ ስንጥል ትክክል ነበርን” ያሉት ፕሬዝዳንት ማክሮን፣ “አሁንም ይህንኑ መድረግ እቀጥላለን” ብለዋል።
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር፤ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ከፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን አስታውቀዋል።
ስታርመር "ለዩክሬን የማይናወጥ ድጋፍን አለን ያሉ ሲሆን፤ በዩክሬን ሉዓላዊነት እና ደህንነት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን" ብለዋል።
የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ክራይተርሰን በበኩላቸው “ስዊድን ከዩክሬን ጋር ትቆማለች፤ ዩክሬን የምትታገለው ለነጻነቷ ብቻ ሳይሆን ለመላው አውሮፓውያንም ጭምር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።