ትራምፕ በአውሮፓ ህብረት ምርቶች ላይ የ25 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናገሩ
ፕሬዝዳንቱ አውሮፓ ህብረት የተፈጠረው አሜሪካን ለመናድ ነው ሲል ተድምጠዋል

በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው የታሪፍ ጭማሪ ተሸከርካሪዎች ፣ የምግብ ተዋጽዖ እና ሌሎች ምርቶችን ይመለከታል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ተመርተው ወደ አሜሪካ በሚላኩ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናገሩ፡፡
በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የንግድ ሚዛን ልዩነት ባላባቸው ሀገራት ያለውን ፍትሀዊ ያልሆነ የንግድ ግንኙነትን ለማሻሻል ቃል ገብተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከህገ ወጥ ስደተኝነት እና ከአደንዛዥ እጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ በሜክሲኮ እና ካናዳ ላይ የታሪፍ ጭማሪ ለማድረግ ዝተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሜክሲኮ የደንብር ጥበቃ ወታደሮችን በማሰማራት ህገ ወጥ ስደትን እና የዕጽ ዝውውርን ለመቆጣጠር መስማማቷን ተከትሎ የታሪፍ ጭማሪው ትግበራ እስከ መጋቢት 4 ድረስ ተራዝሟል፡፡
የአውሮፓ ህብረትን በተመለከተ ከህብረቱ የሚላኩ የምግብ እና የተሸከርካሪ ምርቶች አሜሪካውያን ኩባንያዎችን እየጎዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ዶናድ ትራምፕ ባደረጉት ንግግር ህብረቱ አሜሪካን ለመናድ የተፈጠረ ተቋም ነው ብለዋል፡፡
ህብረቱ ፕሬዝዳንቱ ላደረጉት ንግግር በሰጠው ምላሽ የቀጠናዊ የንግድ ትስስር መፈጠር የአሜሪካ ኩባንያዎች በአውሮፓ ገበያ በሰፊው እንዲሳተፉ እድል ፈጥሮላቸዋል ብሏል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ቃል አቀባይ በህጉ መሰረት ግንኙነታችንን ለማስቀጠል ዝግጁ ነን ነገር ግን ይህ የማይሆን ከሆነ ሸማቾቻችንን እና ንግዶቻችንን ለመጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ታሪፍ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣል መንግስት የሚሰበሰበው ግብር ሲሆን ከፍያውን የሚከፍሉት እቃውን የሚያስገቡ ኩባንያዎች ናቸው።
ትራምፕ ቀረጥ የአሜሪካን ምርት ለማሳደግ፣ ገንዘብ ለማሰባሰብ እና ሌሎች ሀገራት የሚያወጡትን አሜሪካን የሚጎዳ ፖሊሲ ለማስቀየር እንደሚጠቀሙበት ቃል ገብተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ስራ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ከቻይና በሚመጡ ዕቃዎች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ ጭማሪ ያደረጉ ሲሆን ከሌሎች ሀገራት የሚገቡ ምርቶች ታሪፍ ማሻሻያ እንዲደረግም አዘዋል፡፡