ትራምፕ በብረት እና አልሙኒየም ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ጣሉ
ከመጋቢት 4 2025 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው ታሪፍ ወደ አሜሪካ ብረት በሚያስገቡ ነጋዴዎች ላይ ጫና ያበረታል ተብሏል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/11/273-120328-steel_167ab0450cc1c2_700x400.jpg)
ለአሜሪካ የብረት ምርት በብዛት የምትልከው ካናዳም መሰል እርምጃ እንድትወስድ እንደሚያደርጋት ተገልጿል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሁሉም የብረት እና አልሙኒየም ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል።
አሜሪካ በሚገቡ የብረት ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪን የሚያስከትለው ውሳኔ ከመጋቢት 4 2025 ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።
ከውጭ ብረትና አልሙኒየም የሚያስገቡ ነጋዴዎች ላይ ጫናን ይፈጥራል የተባለው ታሪፍ ሁኔታዎችን እንደሚያወሳስብ የካናዳ ፖለቲከኞች እየተናገሩ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን ውሳኔው የሀገር ውስጥ ምርትን አሳድጎ ከውጭ የሚገባውን በሂደት የሚያስቀር ነው በሚል የተነሳባቸውን ትችት ተከላክለዋል።
"ይህ ትልቅ ውሳኔ ነው፤ አሜሪካን ዳግም ሀብታም የማድረግ ጅማሮ ነው" ያሉት ትራምፕ፥ አሜሪካ ብረት እና አልሙኒየም በራሷ አቅም ማምረት እንደሚገባት ተናግረዋል።
የ25 በመቶ ታሪፉ በሸማቾች ላይ የዋጋ ጭማሪ ያስከትላል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም "በሂደት መርከሱ አይቀርም" (በአሜሪካ ሲመረት) የሚል አጭር መልስ ሰጥተዋል።
ትራምፕ በቀጣይም በመድሃኒቶች እና ኮምፒውተር ቺፕሶች ላይ ታሪፍ እንደሚጣል ፍንጭ ሰጥተዋል።
አሜሪካ የብረታ ብረት ከውጭ ከሚያስገቡ ሀገራት ቀዳሚዋ ስትሆን፥ ካናዳ፣ ብራዚል እና ሜክሲኮ ቀዳሚዎቹ አቅራቢዎቿ ናቸው።
ካናዳ ብቻ አሜሪካ ባለፈው አመት ካስገባችው አልሙኒየም ግማሹን የምትሸፍን ሲሆን፥ ታሪፉ ተፈጻሚ ከሆነ ከፍተኛ ጫና ያሳድርባታል።
የካናዳ የኢኖቬሽን ሚኒስትር ፍራንሲዮ ፊሊፕ ቻምፓኝ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የጣሉት ታሪፍ "ፍጹም ምክንያታዊ ያልሆነ" ነው ሲሉ ተቃውመውታል።
የካናዳ ብረታ ብረት አምራቾች የሀገራቸው መንግስት በአሜሪካ ላይ የአጻፋ እርምጃ እንዲወስድ እየጠየቁ ነው።
ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው በብረት ምርቶች ላይ የ25 በመቶ በአልሙኒየም ላይ የ15 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ ቢገልጹም ከአውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ጋር ድርድር አድርገው ውሳኔያቸውን መቀልበሳቸው ይታወሳል።
በቅርቡም በካናዳ እና ሜክሲኮ ላይ የጣሉትን ታሪፍ ከሀገራቱ ጋር በተደረሰ ስምምነት ለአንድ ወር ማራዘማቸው አይዘነጋም።
ታሪፍ ምርቶች ከውጭ ሀገራት ሲገቡ የሚጣል የሀገር ውስጥ ግብር ነው።