የትራምፕ በዓለ ሲመት ከ40 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዳራሽ ውስጥ ሊካሄድ ነው ተባለ
በዓለ ሲመቱ በአዳራሽ እንዲደረግ መወሰኑን ተከትሎ ከዚህ በፊት ከነበሩት በዓለ ሲመቶች ጋር ምን ያህል ሰው ተገኘ የሚል ንጽጽር አይኖርም ተብሏል
ትራምፕ "ከጸሎት መርሃግብሩ እና ሌሎች ንግግሮች በተጨማሪ የበዓለ ሲመቱ ንግግር በአሜሪካ ካፒቶል ሮቱንዳ እንዲካሄድ አዝዣለሁ" ብለዋል
የትራምፕ በዓለ ሲመት ከ40 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዳራሽ ውስጥ ሊካሄድ ነው ተባለ።
የተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት በከባድ ቅዝቃዜ ምክንያት ከ40 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ውጭ መካሄዱ ቀርቶ በአዳራሽ ውስጥ እንደሚከናወን ተገልጿል።
"ከአርክቲክ ወደ አካባቢው የመጣ ከባድ ቅዝቃዜ አለ። ሰዎች በየትኛውም መንገድ እንዲጎዱ አልፈልግም" ሲሉ ትራምፕ ትሩዝ በተባለው ማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ገልጸዋል።
ትራምፕ አክለውም "ከጸሎት መርሃግብሩ እና ሌሎች ንግግሮች በተጨማሪ የበዓለ ሲመቱ ንግግር በአሜሪካ ካፒቶል ሮቱንዳ እንዲካሄድ አዝዣለሁ" ብለዋል።
ፕሬዝደንታዊ በዓለ ሲመት በከባድ ቅዝቃዜ ምክንያት በአዳራሽ ውስጥ የተካሄደው የቀድሞው ፕሬዝደንት ሮናልድ ሪገን በ1985 ለሁለተኛ ዙር የስልጣን ዘመናቸው በዓል ሲመት በፈጸሙበት ወቅት ነበር። በወቅቱ የዋሽንግተን ቅዝቃዜ ኔጋቲቭ 10 ደርሶ የነበረ ሲሆን በነገው እለት ደግሞ ኔጋቲቭ 19 እንደሚደርስ የአየር ትንበያ ያመለክታል።
ትራምፕ እንደተናገሩት ደጋፊዎቻቸው የበዓለ ሲመት ስነስርዓቱን በካቲቶል ዋን ግቢ ባሉ ስክሪኖች፣ በእግርኳስ ሜዳዎች እና በሆኪ መጫወቻ ቦታዎች ባሉ ስክሪኖች ማየት ይችላሉ ብለዋል። በፔንስልቬንያ ጎዳና ወደ ዋሽንግተን እንዲያቀኑ እቅድ ተይዞላቸው የነበሩት ማርሽ ባንድና ሌሎች ቡድኖችን ጨምሮ ፕሬዝደንታዊ ትርኢት በካፒቶል ዋን ግቢ እንደሚካሄዱ ትራምፕ ገልጸዋል።
ትራምፕ እንዳሉት በዓለ ሲመት ከፈጸሙ በኋላ የተሰበሰበውን ህዝብ ያገኛሉ። በዓለ ሲመቱ በአዳራሽ እንዲደረግ መወሰኑን ተከትሎ ከዚህ በፊት ከነበሩት በዓለ ሲመቶች ጋር ምን ያህል ሰው ተገኘ የሚል ንጽጽር አይኖርም ተብሏል።
ትራምፕ በ2017 ለመጀመሪያ ጊዜ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ በናሽናል ሞል የተገኘው ህዝብ ቁጥር ባራክ ኦባማ በ2009 ቃለ መሃላ በፈጸሙበት ጊዜ ከነበረው ጋር እንደሚያንስ በሚያመላክቱ የሚዲያ ሪፖርቶች ብስጭታቸውን ገለጸው ነበር።
የመርሃግብሩ ለውጥ ስነስርዓቱን በአካል ለመታደም የሚመጣውን ህዝቡ ቁጥር ይቀንሰዋል። በካቲቶል ሂል በአካል ተገኝተው ስነስርዓቱን እንዲታደሙ ትኬት የተሰጣቸው ከ220 ሺ በላይ ሰዎች በአዳራሽ ገብተው መመልከት አይችሉም።