ጣልያን፣ ስዊዘርላንድ እና አረብ ኢምሬት ደግሞ የሚሊየነሮቹ መዳረሻ ሀገራት ናቸው
ከ10 ሺህ በላይ የብሪታንያ ሚሊየነሮች መሰደዳቸው ተገለጸ።
ከዚህ በፊት አፍሪካን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ ባለጸጋዎች ዋነኛንመዳረሻ የነበረችው ብሪታንያ አሁን ደግሞ እየተሰደዱባት ነው ተብሏል።
በብሪታንያ ስልጣን ላይ ያለው ሊበራል ፓርቲ ከ2026 ጀምሮ የሚተገበር አዲስ የግብር ህግ አስተዋውቋል።
ባለጸጋዎች ካላቸው ሀብት ላይ የ20 በመቶ ግብር እንዲጣል የሚጠይቀው ይህ ህግ በለንደን እና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ያሉ ባለጸጋዎች እንዲሰደዱ ምክንያት መሆኑን ዘ ታየምስ ዘግቧል።
በጠቅላይ ሚንስትር ኬር ስታርመር የሚመራው መንግሥት የሀብት መጠናቸው አንድ ሚሊዮን ፓውንድ እና ከዛ በላይ ሀብት ባላቸው ሰዎች እና ኩባንያዎች ላይ የ20 በነቶ ግብር እንዲከፍሉ ይጠይቃል።
ይህን ተከትሎም በተለይም ለብዙ ዓመታት ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡ ኩባንያዎች በአዲሱ ህግ ደስተኞች እንዳልሆኑም ተጠቅሷል።
እንደ ዘገባው ከሆነ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት ውስጥ ብቻ 10 ሺህ 800 ሚሊየነሮች ብሪታንያን ለቀዋል።
የተሰደዱት ባለጸጋዎች ብዛት በ2023 ዓመት ከነበረው ጋር ሲነጻጸርም በ157 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ባለጸጋዎቹ ከብሪታንያ ወደ ጣልያን፣ ስዊዘርላንድ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት እንደተሰደዱም ተገልጿል።
የባለጸጋዎቹ መሰደድ የብሪታንያን ኢኮኖሚ ይጎዳል የተባለ ሲሆን በተለይም መንግሥት ከግብር የሚሰበስበውን ገቢ ከመቀነሱ ባለፈ የስራ ቅጥር እና ተያያዥ ችግሮችን ሊያባብስ እንደሚችልም ተገልጿል
ከብሪታንያ በመቀጠልም ቻይና በተጠሰው ተመሳሳይ ዓመት በርካታ ባለጸጋዎቿ ወደ ሌሎች ሀገራት ተሰደዋል ተብሏል።