ዶናልድ ትራምፕ መስክ በአስተዳደራቸው ውስጥ ያላቸው ስልጣን የተገደበ መሆኑን ተናገሩ
ቢሊየነሩ ኢለን መስክ በአዲሱ አስተዳደር ላይ ባለው ከፍተኛ ተጽዕኖ ፕሬዝዳንቱ ሲተቹ ቆይተዋል

ዶናልድ ትራምፕ ከአስተዳደራቸው ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ስብሰባ መስክ ምክረ ሀሳቦችን መሰጠት እንጂ ብቻውን ውሳኔ መወሰን አይችልም ሲሉ መናገራቸው ተደምጧል
በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በአለማችን ቁጥር አንድ ባለሀብት ኢለን መስክ መካከል ስንጥቃት ስለመፈጠሩ የአሜሪካ ሚዲያዎች እየዘገቡ እንደሆነ ይገለጻል፡፡
ቢሊየነሩ በአስተዳደሩ ውስጥ አለው በሚባለው ከፍተኛ ተጽኖ የሰላ ትችት ሰለባ ሆነው የሰነበቱት ፕሬዝዳንቱ በመጨረሻም ለሁኔታው ምላሽ ለመስጠት ወስነዋል፡፡
ትራምፕ ከካቢኔዎቻቸው እና ከሌሎች የመንግስታቸው ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት “ለምትመሩት ዘርፍ ሀላፊ እናንተ እንጂ ኢለን መስክ አይደለም እሱ ምክረ ሀሳቦችን የመስጠት እንጂ በቅጥር ፖሊሲዎቻቸሁ ላይ የመወሰን ስልጣን የለውም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የመንግስት መስርያቤቶችን እና ሰራተኞችን የስራ አፈጻጸም ለመፈተሸ በትራምፕ የተሾመው ኢለን መስክ በመላው አሜሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከመንግስት ስራ እንደሚያፈናቅል እንዲሁም ከፍተኛ የሰራተኛ ቅነሳ እንደሚድርግም በተደጋጋሚ ሲዝት ተስተውሏል፡፡
ከዚህ ባለፈም ፕሬዝዳንቱ ጋዜጣዊ መግለጫ በሚሰጡባቸው እና በተለያዩ መድረኮች በመገኘት ከትራምፕ በበለጠ ዘለግ ላለ ጊዜ ንግግር የሚያደርገው መስክ በአዲሱ አስተዳደር ላይ የማይለካ ተጽኖ ተጎናጽፏል በሚል የተለያዩ ሰዎች እንዲያወሩ በር ከፍቷል፡፡
የቢሊየነሩ እንቅስቃሴ በፍርድ ቤት ፣ በዴሞክራቶች እና በአንዳንድ ሪፐብሊካን ጭምር ተቃውሞን አስተናግዷል፡፡
ይህን ተከትሎ ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ በትላንትናው ዕለት የኢለን መስክን የስልጣን እና ሀላፊነት ደረጃ የሚወስን ወሳኝ ንግግር አድርገዋል፡፡
በአዲስ የፕሬዝዳንቱ መመሪያ መሰረት በሰራተኛ ቅነሳ እና ቅጥር ፣ በፖሊሲዎች እና በሚፈጸሙበት ፍጥነት ሁኔታ ላይ የመጨረሻ ውሳኔዎችን የሚያሳልፉት የካቢኔ ሀላፊዎች እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ ታድሞ የነበረው ኢለን መስክ በፕሬዝዳንቱ መመሪያ እንደሚስማማ እና “ዶጅ” የተሰኘው መንግስታዊ ተቋም የተወሰኑ ስህተቶች መፈጸሙን ማመኑን ፖለቲኮ መጽሄት አስነብቧል፡፡
በአዲሱ የፕሬዝዳንቱ መመሪያ መሰረት በስህተት ከስራቸው የተቀነሱ ሰዎች ወደ ስራቸው እንደሚመለሱ በግልጽ የታወቀ ነገር ባይኖርም ትራምፕ በየሁለት ሳምንቱ መሰል ስብሰባዎች በማድረግ አፈጻጸሙን እንደሚገመግሙ ቃል ገብተዋል፡፡
በሌላ በኩል ግዙፍ የመንግስት ተቋማት ተቋማቸውን በመገምገም አላስፈላጊ ሰራተኞችን እና የስራ ክፍሎችን የማይቀንሱ ከሆነ ኢለን መስክ ይህን የማድረግ ሀላፊነት እንዳለው አረጋግጠዋል፡፡
ትራምፕ ጠንካራ ሰራተኞችን በአስተዳደራቸው ውስጥ ማቆየት እንደሚፈልጉ ቢናገሩም አስተዳደራቸው በቅርብ ሳምንታት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን ከተለያዩ የመንግስት ኤጄንሲዎች አሰናብተዋል፡፡
የተለያዩ የዴሞክራት ፓርቲ አባላት የትራምፕ የሰራተኞች ቅነሳ ከአፈጻጸም እና ከስራ አቅም ጋር የሚገናኝ ሳይሆን የዜጎችን መብት በግልጽ የሚጥስ ድርጊት ነው ሲሉ በተደጋጋሚ አውግዘውታል፡፡