የትራምፕ አስተዳደር ደርዘን ገደማ የአሜሪካ የውጭ የዲፕሎማሲ ተልእኮዎችን ሊዘጋ መሆኑ ተገለጸ
ፕሬዝደንት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው "ተአማኒና ውጤታማ" በሆነ መልኩ እንዲፈጸም የአሜሪካ የውጭ አገልግሎት እንዲገመገም ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ይታወሳል

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመላው አለም ያሉ 70ሺ ገደማ ሰራተኞች ያሏቸውን 270 የዲፕሎማቲክ ተልእኮዎችን እንደሚመራ በጽረ-ገጹ አስፍሯል
የትራምፕ አስተዳደር ደርዘን ገደማ የአሜሪካ የውጭ የዲፕሎማሲ ተልእኮዎችን ሊዘጋ መሆኑ ተገለጸ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቀጣይ ወራት በተለይ በምዕራብ አውሮፓ ያሉ ደርዘን ገደማ ቆንስላዎችን ለዝጋትና በአለምአቀፍ ደረጃ ያሉትን ሰራተኞች ለመቀነስ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ሮይተርስ በርካታ የአሜሪካ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በዋና መስሪያቤቱ ስር በሰብአዊ መብት፣ በስደተኞች፣ በአለምአቀፍ የወንጀል ፍትህ፣ በሴቶች፣ በአለምአቀፍ የሰዎች ዝውውርና በመሳሳሉ ጉዳየች የሚሰሩ ሰራተኞች ያለባቸውን ቢሮዎች ወደ አንድ ለማጣመር እየሰራ ነው።
በመላው አለም ያሉ የአሜሪካ ተልእኮዎች አሜሪካውያንንና የሀገር ውስጥ ሰራተኞችን በ10 በመቶ እንዲቀንሱ መጠመቃቸውን ባለፈው ወር መዘገቡን ሮይተርስ አስታውሷል። ፕሬዝደንት ትራምፕና ቢሊየነሩ ኢለን መስክ ወጭ ለመቀነስ የአሜሪካ የስለላ ድርጅትን(ሲአይኤን) ጨምሮ የፌደራል የመንግስት መስሪያቤት ሰራተኞች በከፍተኛ ቁጥር እያባረሩ ይገኛሉ።
የሪፐብሊኩ ፕሬዝደንት ትራምፕ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሁኔታ "ቅድሚያ ለአሜሪካ" ከሚለው ፖሊሲያቸው ጋር የተጣመመ መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ። ፕሬዝደንት ባለፈው ወር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው "ተአማኒና ውጤታማ" በሆነ መልኩ እንዲፈጸም የአሜሪካ የውጭ አገልግሎት እንዲገመገም ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት ታማኝ ያልሆኑ ሰራተኞችን በማባረር እንቅፋት የሚሆንባቸውን አሰራር እንደሚያጸዱ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ተችዎች እንደሚሉት ከሆነ የአሜሪካ የዲፕሎማሲ ሰራተኞች ቅነሳ በመላው አለም በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ዋጋ ያለው እርዳታ ከሚያሰራጨው የአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት(ዩኤስኤአይዲ) መዘጋት ጋር ተዳምሮ ቻይና ሩሲያን ለመሳሰሉ ተቀናቃኞች አደጋኛ ክፍተት የሚፈጥር ነው ይላሉ።
ትራምፕና አጋራቸው መስክ የአሜሪካ መንግስት እጅግ ትልቅ ነው፤የአሜሪካውያን ግብፍ ከፋዮች ገንዘብ ያለአግባብ እንዲባክንና እንዲጭበረበር ምክንያት ሆኗል ይላሉ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመላው አለም ያሉ 70ሺ ገደማ ሰራተኞች ያሏቸውን 270 የዲፕሎማቲክ ተልእኮዎችን እንደሚመራ በጽረ-ገጹ አስፍሯል።