ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ የመከላከያ በጀት እንዲቀነስ ትዕዛዝ ሰጡ
ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች የፔንታጎን ወጪን እስከ 8 በመቶ የሚቀንስ እቅድ እንዲያዘጋጁ አዘዋል

እቅዱ ተግባራዊ መሆን ሲጀምር በአምስት አመታት ውስጥ 290 ቢሊየን ዶላር የወጪ ቅናሽን እንደሚያስከትል ተነግሯል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመከላከያ በጀትን መቀነስ የሚያስችል እቅድ እንዲዘጋጅ አዘዙ፡፡
አዲሱ የበጀት ቅነሳ የመከላከያ በጀት እና የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር መስርያ ቤት ፔንታጎን ወጪን መቀነስ አላማው ያደረገ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በሰጡት ትዕዛዝ የፔንታጎን ከፍተኛ ባለስልጣናት ከሀገሪቱ የመከላከያ በጀት ላይ በአመት እስከ 8 በመቶ ድረስ ቅናሽ ለማድረግ የሚያስችል እቅድ የሚያዘጋጁ ይሆናል፡፡
እቅዱ ተግባራዊ መሆን ሲጀምር በአምስት አመታት ውስጥ 290 ቢሊየን ዶላር የወጪ ቅናሽን እንደሚያስከትል ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።
የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሰት በሰጡት መግለጫ ፔንታጎን እነዚህን ዋና ዋና ቅነሳዎች ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ አለበት ብለዋል።
የወጪ ቅነሳው በተለያዩ መንገዶች የሚደረግ ሲሆን አላስፈላጊ ግዢዎችን እና ወታደራዊ ድጋፎችን ማቋረጥ የስራተኛ ቅነሳ እና ሌሎች የወጪ ቅነሳ መንገዶችን ሊከተል እንደሚችል ተነግሯል፡፡
ዋሽንግተን ፖስት በምንጭነት ከጠቀሳቸው አካላት አገኝሁት ባለው መረጃ መሰረት በታችኛው እርከን ላይ የሚገኙ የሲቪል ሰራተኞች በሰራተኛ ቅነሳው ኢላማ ሊደረጉ ይችላሉ፡፡
ፔንታጎን በአሁኑ ወቅት 900 ሺህ የሲቪል ሰራተኞችን ፣ 1.3 ሚሊየን ወታደሮችን እንዲሁም 800 ሺህ የብሔራዊ ዘብ እና ተጠባባቂ ጦሮችን ያስተዳድራል፡፡
የትራምፕ አስተዳደር የሜክሲኮ ድንበር ጥበቃ፣ የኒዩክሌር ማሻሻያ ግንባታ፣ የኢንዶ-ፓሲፊክ ማዘዣ እና የጠፈር ምርምር ድጋፍን ጨምሮ 17 ዘርፎች ከውጪ ቅነሳው ውጭ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
በአንፃሩ የመካከለኛው ምስራቅ ስራዎችን የሚቆጣጠሩት የአውሮፓ እና የአፍሪካ ማዘዣዎች ቅነሳው የሚመለከታቸው ይሆናል፡፡
አሜሪካ ለ2025 የመከላከያ በጀት 850 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በጀት ይዛለች፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሰት አዲስ የወጪ ቅነሳ ሰራዊቱን መልሶ ለመገንባት እና ለማቋቋም እንዲሁም መከላከያው ያለበትን ክፍተት በዝርዝር ለማወቅ ያግዛል ብለዋል፡፡
የህግ አውጭዎች በበኩላቸው በተለይም ከቻይና እና ሩሲያ የሚመጡ አደጋዎችን ለመቋቋም ከፍተኛ ወታደራዊ በጀት መያዝ እንደሚያስፈልግ እየጠየቁ ነው ።
ትራምፕ ለማድረግ ያሰቡት ወታደራዊ በጀት ቅነሳ ሀገሪቷን ተጋላጭ ሊያደርጋት እንደሚችም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡