በአሜሪካ - ሜክሲኮ ድንበር ተጨማሪ 10 ሺህ ወታደሮች ሊሰማሩ ነው
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ህገ ወጥ ስድተኞቸን ለመከላከል በያዙት ጠንካራ አቋም በደቡባዊ ድንበር የአስቸኳያ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል
ለፔንታጎን የቀረበው የወታደር ስምሪት ሰነድ በድንበር አቅራቢያ የሚገኙ የጦር ካምፖች ለስደተኞች ማቆያነት ክፍት እንዲሆኑ ይጠይቃል
የትራምፕ አስተዳደር እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ወታደሮችን ወደ አሜሪካ ሜክሲኮ ድንበር ለማሰማራት በማጤን ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
አስተዳደሩ በድንበሩ አቅራቢያ የሚገኙ ወታደራዊ ካምፖችን ከሀገር የሚወጡ እና በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የሚያቋርጡ ስደተኞችን ለማቆያነት ለመጠቀም አስቧል፡፡
ትራምፕ ሰኞ እለት ስራ ሲጀምሩ በፈረሙበት የስራ አስፈፃሚ ትዕዛዝ በደቡብ ድንበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የሀገር ውስጥ ደህንንት (ሆምላንድ ሴኩሪቲ) ስደተኞችን ለመከላከል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የመከላከያ ሚኒስቴር ወታደሮችን እና አስፈላጊ ግብአቶችን በማሟላት እንዲያግዝ አዘዋል፡፡
የዋይት ሀውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት በትላንትናው ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት 2500 ወታደሮች ሰፍረው ወደሚገኙበት ደቡባዊ ድንበር ፕሬዝዳንቱ 1500 ወታደሮችን እንዲሰማሩ ተጨማሪ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
ስምሪቱ 1 ሺ ወታደሮችን እና 500 የባህር ሀይል አባላትን የሚያካትት ሲሆን በተጨማሪም ወደ ካሊፎርኒያ እና ቴክሳስ ግዛት ትላልቅ የጦር ሄሊኮፕተሮች ማሰማራትን ይጨምራል ተብሏል፡፡
ቴክሳስ እና ሌሎች ግዛቶች ከሜክሲሶ ጋር የሚያዋስናቸውን ድንበር በአደገኛ አጥር ከማጠር ጀምሮ የብሔራዊ ጥበቃ ወታደሮች እንዲሰማሩ ፈቃድ ሰጥተዋል፡፡
ሆኖም ቀደም ብሎ ተግባራዊ የተደረጉ እና አሁንም እየተካሄዱ የሚገኙ የድንበር ጥበቃ እንዲሁም የህገወጥ ስደት መከላከል ስራዎች ተጨማሪ ሀይል ስለሚያስፈልጋቸው ትራምፕ 10 ሺህ ወታደሮች በደቡባዊ ድንበር እንዲሰማራ ከአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ፔንታጎን ጋር እየመከሩ ይገኛሉ፡፡
ለውይይት በቀረበው ሰነድ ላይ በአቅራቢያው የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ካምፖች በህገወጥ መንገድ ድንበር የሚያቋርጡ ስደተኞችን ለመያዝ እንዲችሉ ተደርገው እንዲመቻቹ ሀሳብ አቅርቧል፡፡
የስደተኛ ማቆያዎቹ እያንዳንዳቸው 1 ሺህ ሰዎችን መያዝ የሚችሉ 14 ማቆያዎች እና ተጨማሪ 10 ሺህ ሰዎችን ማቆየት የሚያስችሉ 4 ካምፖች እንዲዘጋጁ ነው ሰነዱ የሚጠይቀው፡፡
ወታደሮቹ በቀጥታ ህግ ማስከበር ላይ ከመሳተፍ ይልቅ የድንበር ማገጃ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ፣ የአሰሳ እና ቅኝት እንዲሁም በማቆያ ውስጥ የሚገቡ ስደተኞች ጥበቃ ላይ እንደሚያተኩሩ ሲቢኤስ አስነብቧል፡፡