አሜሪካ ዘለንስኪን ለመተካታ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር በድብቅ ውይይት መጀመሯ ተሰማ
ቮለድሚር ዘለንስኪ በአሁኑ ወቅት በሀገራቸው ዜጎች ያላቸው የተቀባይነት ደረጃ 44 በመቶ ነው

ዋሽንግተን በዩክሬን ምርጫ እንዲደረግ ግፊት እያደረገች መሆኗን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪን ሊተኩ ከሚችሉ የፖለቲካ ሰዎች ጋር ነው እየመከረች የምትገኘው
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ደጋፊዎች የዩክሬንን ፕሬዝዳንት ቮለደሚር ዘለንስኪን ከሚቃወሙ የፖለቲካ መሪዎች ጋር ሚስጥራዊ ውይይት መጀመራቸው ተነግሯል፡፡
ፖለቲኮ ጋዜጣ ይዞት በወጣው ዘገባ በጦርነቱ ምክንያት በተጣለው ወታደራዊ አስተዳደር (ማርሻል ሎው) ምክንያት ተራዝሞ የነበረው ምርጫ በቅርቡ እንዲደረግ ግፊት እደረገች የምትገኘው አሜሪካ ዘለንስኪን የሚተካ መሪ በማፈላለግ ላይ ትገኛለች ብሏል፡፡
እነዚህ ሚስጥራዊ ስብሰባዎች የተካሄዱት የአሜሪካ እና የዩክሬን ፍጥጫ እየጨመረ በሚገኝበት ወቅት የዘለንስኪን አማራጭ ለመፈለግ ሲሆን ይህም የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡
ፖለቲኮ ጋዜጣ ማንነታቸውን ካልጠቀሳቸው ምንጮች ባገኘው መረጃ ሚስጥራዊ ስብሰባዎቹ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ ፓርቲ ታዋቂ ሰዎች እና በፖለቲካዊ ፍላጎቷ ለረጅም ጊዜ ከምትታወቀው የቀድሞዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዩሊያ ቲሞሼንኮ እና ሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች ጋር የተደረጉ ናቸው፡፡
ድርጊቱን የተቃወሙ ሰዎች በተለይም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን በጦር ግንባር እየተፋለሙ በሚገኙበት እና በውጭ አገር በስደት በሚኖሩበት ጊዜ ይህ እርምጃ ትርምስ በማስከተል የሩሲያን ጥቅም እንደሚያስከብር እየተከራከሩ ነው፡፡
የትራምፕ ቡድን በበኩሉ በጦርነት እና በሙስና የተዳከመው የዩክሬን ህዝብ እድሉን ካገኘ ዘለንስኪን ከስልጣን ሊያወርድ የሚችል ድምጽ ሊሰጥ እንደሚችል ያምናል።
የዩክሬን የፖለቲካ መሪዎችን አናግረዋል ከተባሉት የአሜሪካ ባለስልጣናት መካከል አንዱ የሆኑት የአሜሪካ የንግድ ሚንስትር ሃዋርድ ሉትኒክ ትራምፕ በዩክሬን ፖለቲካ ውስጥ ማንኛውንም አይነት ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት አንደማያደርጉ ቢክዱም፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እና አጋሮቻቸው የሚሰጡት መግለጫ በዘለንስኪ ላይ ግልፅ የሆነ ጫና እያሳደሩ እንደሚገኝ አመላካች መሆኑ ይነሳል፡፡
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ዘለንስኪን ያለ ምርጫ የሚመራ አምባገንን ሲሉ መወረፋቸው ይታወሳል፡፡
በቅርቡ በዋሽንግተን በሁለቱ መሪዎች መካከል ከተካሄደው ፍጥጫ የተሞላበት ክርክር በኋላ ደግሞ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዩክሬን ለሰላም ዝግጁ የሆነ አማራጭ መሪ ያስፈልጋታል ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ዘለንስኪ በቅርቡ በርካታ ፈተናዎችን እስተናገዱ ቢሆንም የቅርብ ጊዜ የህዝብ አስተያየቶች ዘለንስኪ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች በተሻለ የህዝብ ተቀባይነት እንዳላቸው የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
የትራምፕ አስተዳደር ምርጫ የሚደረግ ከሆነ ዘለንስኪ ከስልጣን ሊነሱ እንደሚችሉ ቢያምንም የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ፕሬዝዳንቱን ሊገዳደር የሚችል ጠንካራ አማራጭ እንደሌለ መናገራቸውን ፖለቲኮ አስነብቧል፡፡
በቅርብ ጊዜ በተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየቶች መሰረት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ 44 በመቶ የዩክሬናውያን ድጋፍ ሲኖራቸው ፣ የእርሳቸው ዋና ተቀናቃኝ በብሪታንያ የዩክሬን አምባሳደር እና ወታደራዊ መሪ ቫለሪ 20 በመቶ ፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ 10 በመቶ ተቀባይነት ሲኖራቸው ፣ ዩሊያ ቲሞሼንኮ በበኩላቸው ከ 5.7 በመቶ መብለጥ አልቻሉም፡፡
እነዚህ የምርጫ እውነታዎች የዩክሬን ተቃዋሚዎች በፖለቲካዊ ምኅዳሩ ላይ እውነተኛ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል እጩን ለማቅረብ ያላቸውን ችሎታ በተመለከተ ጥያቄዎችን አስነስተዋል፡፡
የትራምፕ አስተዳደር ጊዜያዊ የተኩስ አቁምን ከፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በኋላ ለማድረግ እና ከዚያም ወደ አጠቃላይ የሰላም ድርድር ለመጓዝ ይፈልጋል፤ ይህ ሁኔታ በአብዛኛው ከሞስኮ ፍላጎቶች ጋር የሚጣጣም ነው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዘለንስኪ የስልጣን ጊዜያቸውን በመጨረሳቸው ህጋዊ መሪ ናቸውው ብለው እንደማይቀበሉ ከዚህ ቀደም መናገራቸው ይታወሳል፡፡