ትራምፕ በዘንድሮው ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ለዩክሬን የሚደረገውን ወታደራዊ ድጋፍ ሊያቋርጡ ይችላሉ ተባለ
የቀድሞ ፕሬዝዳንት ስልጣን የሚይዙ ከሆነ ቀዳሚ ተግባራቸው የምስራቅ አውሮፓውን ግጭት ማስቆም እንደሆነ ተናግረዋል
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለመደራደር ፍቃደኛ ካልሆች አሜሪካ የምትሰጠውን ወታዳራዊ ድጋፍ ታቋርጣለች ነው የተባለው
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዘንድሮ ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ እንደሚያቋርጡ የደህንነት አማካሪዎቻቸው ተናግረዋል፡፡
የትራምፕ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሊውተነንት ጄነራል ኬት ኪሎግ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መቋጫ ስትራቴጂን አዘጋጅተው ለትራምፕ ማቅረባቸውን ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ስትራቴጂ ጦርነቱን ሊያስቆሙ የሚችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች የተቀመጡ ሲሆን ከነዚህ መካከል ሁለቱን ተዋጊዎች በየትኛውም መንገድ ወደ ድርድር መድረክ ማምጣት የሚለው የመፍትሄ ሀሳብ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት፡፡
ዩክሬን ለመደራደር ፈቃደኛ ካልሆነች አሜሪካ ወታደራዊ ድጋፏን የምታቆም ሲሆን በአንጻሩ ሩሲያ እምቢተኝነትን ካሳየች ለዩክሬን ገደብ የሌለው የጦር መሳርያ ድጋፍ እንደሚደረግ በስትራቴጂው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ትራምፕ ከመገናኛ ብዙሀን ጋር በነበራቸው ቆይታ እና በምርጫ ቅስቀሳ መድረኮች ላይ እርሳቸው በስልጣን ላይ ቢሆኑ ሩሲያ ዩክሬንን እንደማትወር በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት አሁኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆባይደን የሩስያ እና የዩክሬንን ጦርነት የያዙበት መንገድ ወደ ሶስተኛው የአለም ጦርነት የሚወሰድ ነው ሲሉም ይተቻሉ፡፡
ዩክሬን ሩሲያን የማሸነፍ አቅም የላትም ብለው የሚያምኑት ትራምፕ ጦርነቱን ለማቆም ሁለቱን ወገኖች አስቀምጦ ማደራደር መፍትሄ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
“የጆ ባይደን አስተዳደር ለዩክሬን በአሜሪካ ታክስ ከፋዮች ገንዘብ ያስታጠቀው የጦር መሳሪያ የጦርነቱን ውጤት ሊቀይረው አልቻለም ፤ስለዚህ መጨረሻው ላልታወቀ ጦርነት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማደረግ ከኪሳራ የዘለለ ውጤት የለውም” ያሉት የትራምፕ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጄነራል ኪሎግ ናቸው::
አማካሪው አክለውም ጦርነቱን ለማስቆም መፍትሄው ሁለቱን ሀገራት ልዩነቶቻቸውን አጥብበው እንዲቀራረቡ ማደረግ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ከ2017-2021 በነበረው የትራምፕ የስልጣን ዘመን በብሔራዊ ደህንት አማካሪነት ያገለገሉት ሊውተነንት ጄነራል ኪሎግ በተኩስ አቁም የሚጀምረው በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል የሚደረገው የሰላም ድርድር ቀጥሎም ወደ ዘላቂ ጦርነት ማቆም እንዲገቡ ፣ የኔቶ የአባልነት ጥያቄን ጨምሮ በድንበር ጉዳዮች ላይ እንዲደራደሩ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
ይህ በትራምፕ የደህንነት አማካሪዎች የተዘጋጀው የጦርነት ማቆም ስትራቴጂ አሜሪካ በቀጠናው የምታሳልፈው ትልቁ ውሳኔ መሆኑን ተከትሎ ወደ ተግባራዊነት የሚቀየር ከሆነ ተቃውሞዎችን ሊያስተናግድ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
ትራምፕ በዚህ ስትራቴጂ የዋሽንግተን የቅርብ አጋር ከሆኑ አውሮፓውያን እና ከራሳቸው ሪፐብሊካን ፓርቲ ሊገጥማቸው የሚችለው ተቃውሞ ተጠቃሽ ነው፡፡
ትራምፕ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪዎቻቸው ባቀረቡት ስትራቴጂ ዙርያ ይፋዊ ማብራርያ አልሰጡም።
ነገር ግን በምርጫው የሚያሸንፉ ከሆነ ይህን ስትራቴጂ ባይቀበሉ እንኳን አሜሪካ በራሷ ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለባት በሚለው አካሄዳቸው ለዩክሬን የሚደረገውን የጦር መሳርያ ድጋፍ ሊቀንሱ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡
አሜሪካ እስካሁን ለዩክሬን 70 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው ወታደራዊ ድጋፎችን አድርጋለች፡፡