የአሜሪካ ተወካዮች ምክርቤት ለዩክሬን የ61 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አጸደቀ
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የዋሽንግተን ድጋፍ ዩክሬናውያንን ከሞት የሚታደግ ነው በሚል ምስጋናቸውን አቅርበዋል
ሩሲያ በበኩሏ ድጋፉ “አሜሪካን የሚያበለጽግና የዩክሬናውያንን ሞት የሚያባብስ ነው” ብላለች
የአሜሪካ ተወካዮች ምክርቤት ለዩክሬን፣ እስራኤልና ታይዋን የ95 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አጸደቀ።
ከዚህ ድጋፍ ውስጥ 60.84 ቢሊየን ዶላሩ ከሁለት አመት በላይ ከሩሲያ ጋር እየተዋጋቸ ለምትገኘው ዩክሬን የሚሰጠ ነው ተብሏል።
ረጅም ጊዜ የወሰደው የድጋፍ ህግ በቀጣይ ሳምንት ለህግ መወሰኛ ምክርቤቱ ቀርቦ ከጸደቀ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፊርማቸውን አሳርፈውበት ተፈጻሚ እንደሚሆን ተገልጿል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የአሜሪካ ተወካዮች ምክርቤት ድጋፉን ማጽደቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ዩክሬናውያንን ከሞት የሚታደግና ከሩሲያ ጋር እየተካሄደ ያለውን ጦርነት እንዲቋጭ የሚያደርግ ነው በሚል ምስጋቸውን አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንቱ የዋሽንግተን ድጋፍ “ጦርነቱን እንዳይስፋፋ እና ሀገራችን ጠንካራ የሚያደርግ ነው” ሲሉም በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ከ61 ቢሊየን ዶላር ድጋፉ ውስጥ 23 ቢሊየኑ በዩክሬን የሚገኙ የአሜሪካ የጦር መሳሪያዎች እና ጣቢያዎችን ለማጠናከርና የጎደሉ ግብአቶችን ለማሟላት የሚውል ነው ተብሏል።
7.8 ቢሊየን ዶላር ደግሞ በቀጥታ ለበጀት ድጋፍ እንደሚውል የዩክሬን የገንዘብ ሚኒስትር ሰርጊ ማርቼንኮ መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ሩሲያ ግን የአሜሪካ ተወካዮች ምክርቤት ያጸደቀው ድጋፍ ጦርነቱን ከማባባስ ውጪ ፋይዳ እንደማይኖረው ገልጻለች።
የክሬምሊን ቃልአቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “ድጋፉ አሜሪካን ነው የሚያበለጽገው፤ ዩክሬንን ይበልጥ ያፈራርሳታል፤ የዩክሬናውያንን ሞትም ቢብስ እንጂ አይቀንስም” በሚል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በበኩላቸው፥ አሜሪካ ድጋፉን ያጸደቀችው “ሩሲያን በመፍራት በሽታ ወይም ልክፍት” በመጠቃቷ ነው” ያሉ ሲሆን፥ ድጋፉ ሩሲያን ድል ከማድረግ እንደማይገታት አብራርተዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫም ለዩክሬን፣ እስራኤልና ታይዋን የሚደረገው ድጋፍ በአለማቀፍ ደረጃ ቀውስ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
“ለዩክሬን የሚደረግ ወታደራዊ ድጋፍ ሽብርተኝነትን በቀጥታ እንደመደገፍ ይቆጠራል” ሲሉም በቴሌግራም ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በጦር መሳሪያ በተለይ ተተኳሽ እጥረት እጀምረዋለው ያለችው የመልሶ ማጥቃት የተጓተተባት ዩክሬን ግን ይህን ድጋፍ አጥብቃ ትፈልገዋለች።