አሜሪካ በትግራይ ያለው ግጭት እንዲያበቃ ከኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ጋር እየሰራሁ ነው አለች
ቲቦር ናዥ በትግራይ የተቋረጠው የቴሌኮሙኒኬሽን ግንኙነት እንዲጀምር በመንግስት ላይ ጫና እያደረግን ነው ብለዋል
አሜሪካ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ዜጎቿን ከትግራይ ለማስወጣት እየሰራች መሆኗን ቲቦር ናዥ ገለጹ
አሜሪካ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ዜጎቿን ከትግራይ ለማስወጣት እየሰራች መሆኗን ቲቦር ናዥ ገለጹ
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሃፊ የሆኑት ቲቦር ናዥ እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ራይነር የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታዎች በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች የኦን ላይን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ቲቦር ናዥ ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ዕለት ጀምሮ ሁኔታውን በቅርበት ስንከታተል ስጋታችንን ስንገልጽም ነበር ብለዋል፡
ውጥረቶች በአስቸኳይ ረግበው ጥላቻው ቀርቶ ሰላም እንዲሰፍን በጽኑ ሲያሳስቡ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
የዜጎች ደህንነት መጠበቅ እና ሰላማዊ መሆን እጅጉን አስፈላጊ በመሆኑ ለአሜሪካ ዜጎች ቅድሚያ በመስጠት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ከትግራይ ለማስወጣት በኤምባሲው በኩል በቅርበት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ህወሓት አሁንም ቀጥሎ በመካሄድ ላይ ያለው ውጊያ ዓለማቀፋዊ መልክ ለማስያዝ ምን ያህል ፍላጎት እንዳለው ባሳለፍነው ሳምንት የፈጸማቸው ጥቃቶች አመላካች ናቸው እንደ ቲቦር ናዥ ገለጻ፡፡
ለዚህም ኃላፊነት ወስዶ ፈጽሜያቸዋለሁ ያላቸውን የባህርዳር፣የጎንደር እና የአስመራ የሚሳዔል ጥቃቶችን በማሳያነት አንስተዋል፡፡
ተቀባይነት የላቸውም ያላቸውን እነዚህን ጥቃቶች ሁኔታውን የበለጠ እንደሚያባብሱት በማሳሰብ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ማውገዙን አስታውሰዋል፡፡
ኤርትራ አሁንም ታቅባ እንድትቆይ ከመሪዎቿ ጋር እየተገናኘን እያሳሰብን ነውም ብለዋል፡፡
የግጭቱን ማብቂያ ለመዘየድ በአሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ተወካዮችን ጨምሮ ከቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር እየሰራንም ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ የተቋረጠው የቴሌኮሙኒኬሽን ግንኙነት ወደነበረበት እንዲመለስ በመንግስት ላይ ጫና እያደረግን እንገኛለንም ብለዋል፡፡
ለሰብዓዊ ድጋፎች መድረስ አንዲተባበሩ ሁለቱንም አካላት አሳስበናል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
ቲቦር ናዥ የማይካድራውን ጥቃት አውግዘዋል፡፡
በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ግጭት ያመራው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጥቅምት 24 ህወሓት በትግራይ ክልል ባለው የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት አድርሷል፤እርምጃም እንደሚወሰድ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነው፡፡ግጭቱ ከተጀመረ ከሁለት ሳምንት በላይ ሆኖታል፡፡