ሩሲያ በኩርስክ እና በምስራቅ ግንባር እያካሄደች ያለው ውጊያ እንደበረታባት ዩክሬን ገለጸች
"በኩርስክ ግዛት ጠላት ለሶስተኛ ጊዜ ከባድ ጥቃት እያካሄደ ነው" ሲሉ የዩክሬን ጦር ዋና አዛዡ ኦሌክሳንደር ሲርስኪ ገልጸዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2024/12/18/243-152445-img-20241218-142126-397_700x400.jpg)
የአሜሪካ ወታደራዊ ባለስልጣን በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች መገደላቸውንና ማዕረጋቸውም ከተራ ወታደር እስከ ከፍተኛ አዛዥ ድረስ እንደሆነ ተናግረዋል
ሩሲያ በኩርስክ እና በምስራቅ ግንባር እያካሄደች ያለው ውጊያ እንደበረታባት ዩክሬን ገለጸች።
ሞስኮ ኩርስክ የተባለችውን የሩሲያ ግዛት ይዘው ለመቆየት ሙከራ በሚያደርጉት የዩክሬን ኃይሎች ላይ እያደረገች ያለውን ውጊያ ማጠናከሯን እና በዩክሬን ምስራቃዊ የዶኔስስ ግዛት ጫና መጨመሯን የዩክሬን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት ሶስት አመት ሊሞላው እየተቃረበ ሲሆን የዩክሬን ኃይሎች 1700 ኪሎሜትር በሚረዝመው ግንባር ተሰላችተው እና በቁጥር ተበልጠው ይገኛሉ።
"በኩርስክ ግዛት ጠላት ለሶስተኛ ጊዜ ከባድ ጥቃት እያካሄደ ነው" ሲሉ ዋና አዛዡ ኦሌክሳንደር ሲርስኪ ለመንግስት እና ለክልላዊ አስተዳዳሪዎች በኢንተርኔት ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።
ሲርስኪ አክለውም ሩሲያ በጦር ግንባር ከፍተኛ ጉዳት አጋጥሟቸዋል ያሏቸውን የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በብዛት እየተጠቀመች ነው ብለዋል።
የአሜሪካ ወታደራዊ ባለስልጣን በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች መገደላቸውንና ማዕረጋቸውም ከተራ ወታደር እስከ ከፍተኛ አዛዥ ድረስ እንደሆነ ተናግረዋል። የዩክሬን ጦር በትናንትናው ምሽት ባወጣው ሪፖርት በኩርስክ ግዛት 42 ጥቃቶችን መመከቱን ገልጿል።
ዩክሬን ባለፈው ነሐሴ ወር የምዕራብ ሩሲያዋን ኩርስክ ግዛት በማጥቃት ከተቆጣጠረችው ቦታ 40 በመቶውን አጥታለች። ወታደራዊ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ የኩርስክ ጥቃት ረጅም የነበረውን ግንባር የበለጠ እንዲስፋፋ በማድረግ በዩክሬን ወታደሮች ላይ ጫና ፈጥሯል።
ስርስኪ እንዳሉት የሩሲያ ኃይሎች ፈጣን ግስጋሴ እያደረጉ ባለበት የዶኔስክ ግንባር ውጊያው ከብዷል። የሩሲያ ጦር ትኩረት የሎጂስቲክ ማስተላለፊያ የሆነችውን የፖክሮቭስክ ከተማን ለመያዝ ነው ብለዋል ስርስኪ።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር የሩሲያ ኃይሎች ለዩክሬን የብረት ፋብሪካ ግብአት የሚሆን ከሰል የሚመረትባተን ከፖክሮቭስክ በስተሰሜን የምትገኘውን ሀኒቪካ መንደር ተቆጣጥረዋል።
"ዲፕ ስቴት" የተባለው የዩክሬን የጦር ድረ-ገጽም የሩሲያ ኃይሎች ሀኒቪካን መያዛቸውን ሪፖርት አድርጓል።
ሩሲያ ፖክሮብስክን የምትይዝ ከሆነ በከፊል የያዘችዉን የዶኔስክ ግዛትን ሙሉ በሙሉ ለመጠቅለል በር ይከፍታል ተብሏል።
ጦርነቱን በንግግር ለማስቆም የተደረጉ ጥረቶች እስካሁን አልተሳኩም።
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከፕሬዝደንት ዘለንስኪና ፑቲን ጋር እንደሚነጋገሩ እና ጦርነቱን የሚያስቅም እቅድ እንዳላቸው እየተናገሩ ይገኛሉ።