ትራምፕ ፕሬዝዳንትነቱን ለሦስተኛ ዙር እየፈለጉ ይሆን?
ትራምፕ ለ3ኛ ጊዜ ፕሬዝዳንታዊ የሥልጣን ዘመን መወዳደር እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ፍንጭ መስጠታቸውን ተከትሎ ውዝግብ አስነስቷል

የትራምፕ ፍላጎት የፕሬዚዳንትነት ጊዜን በሁለት ዙር ከሚገድበው ከ22 ኛው የአሜሪካ ህገ መንግስት ማሻሻያ ጋር የሚጋጭ ነው ተብሏል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሀገሪቱን ህገ መንግስት በሚጻረር መልኩ ለ3ኛ ጊዜ ፕሬዝዳንታዊ የሥልጣን ዘመን መወዳደር እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ፍንጭ መስጠታቸውን ተከትሎ ውዝግብ አስነስቷል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ኃውስ በተካሄደ የጥቆሮች ታሪክ ወር ክብረ በዓል ላይ ታዳሚዎችን በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት ብወዳደር ምን ይመስላቹዋል ሲሉ የጠየቁ ሲሆን፤ ታዳሚዎችም በጭበጨባ ድጋፋቸውን አሰምተዋል።
የአሜሪካው ጋዜጣ ዋሽንግተን ፖስት እነዚህ አስተያየቶች በቅርብ ቀናት ውስጥ ከትራምፕ እየጨመሩ ከመጡ ንግግሮች ተለየተው አይታዩም ያለ ሲሆን፤ ትራምፕ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ራሳቸውን “ንጉሱ” ብለው መጥራታቸውንም አስታውሷል።
“ሀገሩን የሚታደግ ሕግ አይጥስም” የሚለውን የፈረንሣይ ንጉሠ ነገሥት ናፖሊዮን ቦናፓርት ጥቅስ በመለጠፍም ከሕግ በላይ መሆናቸው የሚጠቁም ፍንጭ ሰጥተዋል ብሏል ጋዜጣው።
ዋይት ሀውስም ትራምፕ ዘውድ ለብሰው የሚያሳይ ምስል ያሳተመ ሲሆን ይህም “ፍፁም ገዥ” መሆናቸውን የሚያመለክት ነው በሚል ትችት አስተናግዷል ነው የተባለው።
የትራምፕ ሶስተኛ ዙር የስልጣን ዘመን ፍላጎት በዴሞከራቶች እና በተወሰኑ ሪፐብሊካኖች ዘንድም ቁጣን ቀስቅሷል ነው የተባለው።
ፖለቲከኞች እና ተንታኞች በትራምፕ ውስጥ እያደገ ያለው አምባገነናዊ ዝንባሌ አደጋ አለው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የቀድሞ የሰራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር ሮበርት ራይች “ዩናይትድ ስቴትስ በፍጥነት ወደ አምባገነንነት እየተሸጋገረች ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የኢሊኖይ ገዥ ጄቢ ፕሪትዝከር በበኩላቸው “በአሜሪካ ውስጥ ነጉስ የሚባል ነገር የለም፣ ለማንም አልሰግድም” ብለዋል።
በሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ ያሉ አንድ አንድ ታዋቂ ሰዎች ትራምፕን በስልጣን ላይ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆይ እንደሚፈልጉ የተናገሩ ሲሆን፤ “በ2028 ትራምፕን እንፈልጋለን የሚሉ መፈክሮችንም” አሰምተዋል።
አንዳንድ የትራምፕ ደጋፊዎች ሕጉ በአሁኑ ጊዜ ይህንን ባይደግፍም እንደገና ለመወዳደር የሚያስችለውን "ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻ" ሊኖር እንደሚችልም ተናግረዋል።
የትራምፕ ፍላጎት የፕሬዚዳንትነት ጊዜን በሁለት ዙር ከሚገድበው ከ22 ኛው የአሜሪካ ህገ መንግስት ማሻሻያ ጋር የሚጋጭ ነው ተብሏል።
በፈረንጆቹ በ1951 የተሻሻለው የአሜሪካ ህ መንግስት አንድ ሰው ከሁለት ዙር በላይ በፕሬዝዳንትነት እንዳይቀጥል የሚገድብ ሲሆን፤ ትራምፕ ይህን ጥሰው እንቅስቀሴ ካደረጉ ህገ መንግስቱን የሚቃረን ይሆናል ተብሏል።