ከዘጠኝ ዓመት በፊት መንታ ልጆቿ የተገደሉባት እናት ድጋሚ መንታ ልጆችን አረገዘች
ሰባት ቦታ በጥይት ቆስላ የነበረችው እናት በተዓምር ከሞት ተርፋ ድጋሚ የልጆች እናት ለመሆን ጥቂት ወራት ይቀራታል

ይህች እናት በቤት ውስጥ ጥቃት ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን የሚደግፍ ተቋም አቋቁማለች
ከዘጠኝ ዓመት በፊት መንታ ልጆቿ የተገደሉባት እናት ድጋሚ መንታ ልጆችን አረገዘች፡፡
ሜጋ ሂያት አሜሪካዊት ስትሆን በፈረንጆቹ 2015 ላይ ከቀድሞ ባለቤቷ ሩሻን ዊልሰን ከተባለ አሜሪካዊ ተጋብተው መንታ ሴት ልጆችን ወልደው ነበር፡፡
ትዳራቸው በሰላ መቀጣል ያልቻለው እነዚህ ባልና ሚስቶች ለመለያየት ይሞክራሉ፡፡ ይሁንና ባልየው ይህን ውሳኔ በመቃወም በሽጉጥ መንታ ልጆቹን ተኩሶ ይገድላቸዋል፡፡
በመቀጠልም የልጆቹን እናት፣ የሚስቱን አባት ከገደለ በኋላ በመጨረሻ ራሱን ተኩሶ መግደሉን የኒዮርክ ፖስት ዘገባ ያስረዳል፡፡
በወቅቱ ሰባት ጊዜ ተተኩሶባት ህይወቷ በተዓምር የተረፈችው ይህች እናት ከአራት ዓመት በፊት አዲስ ህይወት ጀምራለች፡፡
እናትየው በደረሰባት ጉዳት አንድ አይኗን ከማጣቷ ባለፈ ለዓመታት በዊልቸር እና በሰው እርዳታ ብቻ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡
በቤት ውስጥ ጥቃት ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን የሚደግፍ ተቋም በማቋቋም ስትሰራ የቆየችው ይህች እናት ጆሴፍ ጆንሰን ከተባለ ሰው ጋር ጋብቻ መስርታ መንታ ልጆችን እንዳረገዘች ተገልጿል፡፡
የደረሰብኝ ጉዳት የሚገለጽ አይደለም፣ ዳግም እናት መሆኔ ከስብራቴ እንድድን እና ከጸጸት እንድወጣ አድርጎኛል ስትልም ተናግራለች፡፡
ድጋሚ ልጆችን ማቀፍ እንደምችል ማየቴ እና የራሴን ቤተሰብ መገንባቴ ከምንም በላይ ደስታ ሰጥቶኛል የምትለው እናትየው ከባሏጋ በቀጣይ ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን በማደጎ የማሳደግ እቅድ እንዳላቸውም ተናግራለች፡፡