ትራምፕ ከአለም ጤና ድርጅት አባልነት ለመወጣት እቅድ እያዘጋጁ ነው ተባለ
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ድርጅቱ በአለም አቀፍ የጤና ጉዳዮች ከአሜሪካ ይልቅ ወደ ቻይና አድልቷል ሲሉ ወቅሰውታል
ውሳኔው ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ የድርጅቱን አቅም ሊጎዳው እንደሚችል ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው
የተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሽግግር ቡድን አባላት አሜሪካን ከአለም ጤና ድርጅት አባልነት ለማስወጣት እቅድ እያዘጋጁ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
ሮይተርስ ከምንጮች አገኝሁት ባለው መረጃ መሰረት ፕሬዝዳንት በመጀመርያ ቀን የስልጣን ቆይታቸው ከሚያስተላልፏቸው ቁልፍ የፖሊስ ውሳኔዎች መካከል ከድርጅቱ አባልነት መውጣት አንዱ ሊሆን እንደሚችል ተሰምቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግዙፉ የጤና ኤጄንሲ ወረርሽኞችን እና ሌሎች አለምአቀፋዊ የጤና ቀውሶችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ዋሽንግተንን በማግለል ተወቅሷል፡፡
በተጨማሪም በመሰል አለም አቀፋዊ የጤና ጉዳዮች ከአሜሪካ ይልቅ ወደ ቻይና አድልቷል በሚልም በትራምፕ የሽግግር ቡድን ውንጀላ ቀርቦበታል፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት በአዲሱ አስተዳደራቸው ውስጥ ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየርን ጨምሮ የአለም ጤና ድርጅት ላይ ጠንካራ ትችት የሚሰነዝሩ ሀላፊዎችን በማህበረሰብ ጤና ተቋማት ላይ ሹመዋል፡፡
በመጀመርያ የስልጣን ዘመናቸው ትራምፕ ከድርጅቱ አባልነት ለመውጣት ለአንድ አመት ያህል በሂደት ውስጥ ከዘለቁ በኋላ በአዲሱ የጆ ባይደን አስተዳደር ውሳኔው መሻሩ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከሰቱ ድርጅቱ ቻይናን ተጠያቂ ለማድረግ ወደ ኋላ ብሏል። “ድርጅቱ የቻይና አሻንጉሊት ነው” በሚል በትራምፕ ተደጋጋሚ ወቀሳ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡
ከሳምንታት በፊት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ትራምፕ ከድርጅቱ አባልነት ለመውጣት ባሰሙት ዛቻ ዙርያ ተጠይቀው፤ አሜሪካ በአስተዳደር ሽግግር ውስጥ ስለምትገኝ ጊዜ ያስፈልጋታል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ “የትራምፕ አስተዳደር በድርጅቱ አሰራር ዙርያ በሚያነሳቸው ቅሬታዎች ላይ ተቀምጦ ለመነጋገር እድል ይሰጠናል ብለን እናምናለን” ብለዋል፡፡
ሮይተርስ ያነጋራቸው የተለያዩ የጤና ባለሙያዎች የአሜሪካ መውጣት የድርጅቱን አቅም እንደሚያዳክመው ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን የአለም ጤና ድርጅት የአሜሪካን ክፍተት ለመሙላት በክትባት እና በአለም አቀፍ የወረርሽኝ ቁጥጥር ጉዳዮች ዙርያ ወደ ቻይና የሚያዘነብል ከሆነ በጤናው ጉዳይ የዋሽንግተንን አለም አቀፍ ተጽዕኖ ሊጎዳው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡