የኔቶ አለቃ ከፑቲን ጋር እየተዋጉ ያሉትን ዘለንስኪን ክፉኛ ተቹ
ዋና ጸኃፊው ዘለንስኪ በሾልዝ ላይ የሚያቀርቡትን ትችት እንዲያቆሙ መጠየቃቸውን መገናኛ ብዙኻን ዘግበዋል
ሾልዝ ከሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን ጋር ንግግር ማድረጋቸው ሞስኮን በዲፕሎማሲ ለመነጠል የሚደረገውን ጥረት ያዳክማል በሚል ዘለንስኪ ከፍተኛ ቅሬታ አሰምተው ነበር
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በጀርመን ቻንስለር አላፍ ሾልዝ ላይ ያቀረቡት ትችት ምክንያታዊ አይደለም ሲሉ የኔቶ ዋና ጸኃፊ ማርክ ሩቴ ተናግረዋል።
ዋና ጸኃፊው ዘለንስኪ በሾልዝ ላይ የሚያቀርቡትን ትችት እንዲያቆሙ መጠየቃቸውን መገናኛ ብዙኻን ዘግበዋል።
ባለፈው ወር ሾልዝ ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ንግግር ማድረጋቸው ሞስኮን በዲፕሎማሲ ለመነጠል የሚደረገውን ጥረት ያዳክማል በሚል ዘለንስኪ ከፍተኛ ቅሬታ አሰምተው ነበር።
"ዘለንስኪ ሾልዝን መተቸት ማቆም እንዳለበት ብዙ ጊዜ ነገሬዋለሁ። ምክንያቱም ትክክል ነው ብዬ ስለማላስብ ነው" ሲሉ ሩቴ በዛሬው እለት ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ሾልዝ ጀርመን ሰራሽ የሆኑ ታውረስ ክሩዝ የተባሉ ታንኮችን ለዩክሬን ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ዘለንስኪ ቅሬታ አሰምተው ነበር። ነገርግን ሾልዝ ላለመስጠት የወሰኑት ጦርነቱ እንዳይባባስ እና ጀርመን ከሩሲያ ጋር ቀጥተኛ ፍጥጫ ውስጥ እንዳትገባ በማሰብ እንደነበር በወቅቱ አብራርተዋል።
ሩቴ ግን እንደጀርመን ዩክሬን በምትጠቀመው የመሳሪያ አይነት ላይ ምንም ገደብ እንደማይጥሉባት መናገራቸው ተገልጿል።
"በአጠቃላይ ዩክሬን እንዲህ አይነት አቅም እንደሚያስፈልጋት እናውቃለን" ያሉት ሩቴ አጋሮቿ ምን አይነት መሳሪያዎች ይስጧት የሚለውን መወሰን ግን የእሳቸው ኃላፊነት አለመሆኑን በአንጽንኦት ተናግረዋል።
ሞስሶ የምዕራባውያን እርዳታ የሩሲያ ኃይሎች ግባቸውን ከማሳካት እንደማያግዳቸው እና የጦርነቱን የመጨረሻ ውጤት እንደማይቀይረው በተደጋጋሚ እየገለጸች ነው። ክሬሚሊን የምዕራባውያን ወታደራዊ ድጋፍ ጦርነቱን ከማራዘም ያለፈ ሚና አይኖረውም ብሏል።