ትራምፕ የፈረንሳይና ብሪታንያ መሪዎች የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም "ምንም አልሰሩም" ሲሉ ወቀሱ
በቀጣይ ሳምንት ዋይትሃውስ የሚገኙት ማክሮን እና ስታመር በትራምፕ "አምባገነን" ለተባሉት ዜለንስኪ ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው

ሩሲያ የዩክሬንን ድንበር ጥሳ በመግባት ጦርነት ከጀመረች ከነገ በስቲያ ሶስተኛ አመቷን ትይዛለች
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፈረንሳይ እና ብሪታንያ መሪዎች የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም "ምንም አልሰሩም ሲሉ ወቀሱ።
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታመር በቀጣይ ሳምንት በዋይትሃውስ ከትራምፕ ጋር ይመክራሉ።
ማክሮን እና ስታመር በፕሬዝዳንት ትራምፕ "አምባገነን" የተባሉትን የዩክሬን ፕሬዝዳንት "ጀግና" በማለት ወታደሮቻቸውን ወደ ኬቭ ለመላክ እንዳቀዱ እስከመናገር ደርሰዋል።
አሜሪካ እና ሩሲያ ከነገ በስቲያ ሶስተኛ አመቱን የሚደፍነውን ጦርነት ለማስቆም ባለፈው ሳምንት በሪያድ ሲመክሩ ዩክሬን አለመጋበዟ ኬቭ እና የአውሮፓ አጋሮቿን አስቆጥቷል።
ባለፈው ሰኞም በፓሪስ በተካሄደ ጉባኤ አውሮፓውያኑ ለዜለንስኪ ድጋፋቸውን የገለጹ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት እና የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር በዋይትሃውስ ከትራምፕ ጋር በጉዳዩ ላይ ለመምከር ማቀዳቸው መነገሩ ይታወሳል።
ከፎክስ ኒውስ ጋር ቆይታ ያደረጉት ትራምፕ በነጩ ቤተመንግስት የሚቀበሏቸው ሁለቱ የአውሮፓ መሪዎች የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም አንዳችም ጥረት አላደረጉም ቢሏቸውም በግል ግን የሚያደንቋቸው ግለሰቦች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለኬቭ ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ የሚያደርጉት የአውሮፓ ሀገራት ጦርነቱን ማስቆም በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተደጋጋሚ ምክክሮችን ቢያደርጉም ከፑቲን ጋር የሚደረግ ድርድርን እንደማይቀበሉ ይናገራሉ።
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ከብሪታንያ፣ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ጃፓን ጋር በመሆን ሩሲያ የዩክሬንን ድንበር ጥሳ "ወረራ" ከጀመረች ወዲህ ከ20 ሺህ በላይ ማዕቀቦችን በሞስኮ ላይ ጥለዋል።
ሀገራቱ የወታደራዊ ትብብር ስምምነት በመፈራረም በሩሲያ ከ20 በመቶ በላይ መሬቷ የተያዘባት ዩክሬንን አይዞሽ ማለቱን በገፉበት ወቅት አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የያዙት አቋም ስጋት ፈጥሮባቸዋል።
ከሪያዱ የዋሽንግተን እና ሞስኮ ድርድር በኋላ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ከበርካታ ሀገራት መሪዎች የስልክ ጥሪ የደረሳቸው ሲሆን፥ ኬቭ በድርድሩ ውስጥ እንድትሳተፍ ጫና የመፍጠር እንቅስቃሴውም መቀጠሉን ቢቢሲ ዘግቧል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ዜለንስኪ "የመደራደሪያ ካርድ የለውም፤ ስለዚህ በድርድሩ ላይ መሳተፉ ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም" ነው ያሉት ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የክሬምሊን ቃል አቀባይ መስለዋል በሚል የሚተቹት ትራምፕ፥ ጦርነቱ መቆም ያልቻለው ሩሲያ "ከዜለንስኪ ጋር መስማማት የማይቻል ነገር ስለሆነባት ነው" ብለዋል።
ተንታኞች ትራምፕ በዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ላይ የቃላት ውርጅብኝ ያበዙት የኬቭን ውድ ማዕድናት መውሰድ የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ በማለም ነው ይላሉ።
የ78 አመቱ ፕሬዝዳንት ዩክሬን ከዋሽንግተን ለተደረገላት የመቶ ቢሊየን ዶላሮች ወታደራዊ ድጋፍ ካሳ የምትከፍለው በውድ ማዕድናቷ ነው የሚል አቋም ይዘዋል። ፕሬዝዳንቱ ከዩክሬን ከ400 እስከ 500 ቢሊየን ዶላር እንፈልጋለን ብለዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ማዕድናቱን ለአሜሪካ አሳልፎ መስጠት "ሀገር መሸጥ ነው" በሚል እንደማይቀበሉት ገልጸው የነበረ ቢሆንም ጫናው እየበረታ ሲመጣ ስምምነት ለመፈራረም መቃረባቸውን አስታውቀዋል።
የዋይትሃውስ የደህንነት አማካሪ ማይክ ዋልትዝ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ "ዜለንስኪ ስምምነቱን ይፈርማል" ብለዋል።