አሜሪካ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይፋ የምታደርገው አዲስ ቪዛ ምንድን ነው?
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከግሪን ካርድ በተጨማሪ "ጎልደን ካርድ ቪዛ" ይፋ አድርገዋል

አዲሱ ቪዛ ወደ አሜሪካ የሚገቡ የውጭ ዜጎችን ቁጥር በመጨመር አዳዲስ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያለመ ነው
አሜሪካ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይፋ የምታደርገው አዲስ ቪዛ ምንድን ነው?
ከሁለት ወር በፊት 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ስልጣን የተረከቡት ዶናልድ ትራምፕ በስደተኞች ላይ ጥብቅ ፖሊሲዎችን እንደሚከተሉ ተናግረው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ በተለይም አስቀድመው ወደ አሜሪካ የገቡ እና ህጋዊ መኖሪያ የሌላቸው ስደተኞችን ወደመጡበት በሀይል መመለስን ዋነኛ ስራቸው አድርገዋል።
ባለፉት 60 ቀናት ውስጥም በየዕለቱ ከአንድ ሺህ በላይ ህገወጥ ስደተኞችን እያሰረ ያለው የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳድር አሁን ደግሞ አዲስ ቪዛ ለመስጠት ያሰቡትን እቅድ ይፋ አድርገዋል።
ከሁለት ሳምንት በኋላ መተግበር ይጀምራል የተባለው ይህ አዲስ እቅድ "ጎልደን ቪዛ ካርድ" የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
አዲሱ ቪዛ በተለይም በመላው ዓለም ያሉ ባለጸጎች ወደ አሜሪካ እንዲመጡ ታስቦ እንደተዘጋጀ ተገልጿል።
አመልካቾች ይህን ቪዛ ለማግኘት አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚያስከፍል ሲሆን ይህ ቪዛ አገልግሎት ለአሜሪካዊያን ስራ እድል መፍጠር፣ ኩባንያዎችን ማቋቋም እና አዲስ ኢንቨስትመንት መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ ዘግቧል።
"ጎልደን ቪዛ ካርድ" በአውሮፓ እና አሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባቸው ሩሲያዊያን ባለጸጋዎችን ትኩረት ሊስብ እንደሚችልም ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያዊያን ላይ ስለተጣለው ማዕቀብ ሲጠየቁ " አዲሱ ጎልደን ቪዛ ሩሲያዊያን ባለጸጎችንም ሊጠቅም ይችላል ፣ ጥሩ ሩሲያዊያን እንዳሉ አውቃለሁ" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ወደ አሜሪካ የሚገቡት ባለጸጎች የመንግስትን ወጪ እንዲቀንስ ይረዱናል" ብለዋል።
የአሜሪካ ፌደራል መንግስት ያለበት እዳ 36 ትሪሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ይህም በዓለማችን ካሉ ሀገራት ሁሉ በመጠን ትልቁ ነው።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር በመንግስት ወጪ መጨመር እየተፈተኑ ሲሆን እፎይታ ለማግኘት ሲሉም በባለጸጋው ኢለን መስክ የሚመራ ተቋም አቋቁመዋል።
ይህ ተቋም የመንግስት ተቋማት ሰራተኞቻቸውን እንዲቀንሱ፣ የውጭ እርዳታዎች እንዲቆሙ እና ሌሎች እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል።