የቱኒዚያ ጠቅላይ ሚኒስተር ከኮቪድ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ሁከት ከስልጣናቸው ተነሱ
የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት ካይስ ሰይድ የሀገሪቱን ፓርላማ ከስራ አግደዋል
የፕሬዚዳንት ካይስ ሰይድ ተግባር “መፈንቅለ መንግስት ነው” ሲሉ ተቃዋሚዎች ገልጸዋል
የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት ካይስ ሰይድ ከኮቪድ 19 ሳቢያ በሀገሪቱ የተከሰተውን አመጽ ተከትሎ የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከኃላፊነት ማንሳታቸው ተሰምቷል።
በተጨማሪም በመላው ቱኒዚያ የተከሰተውን አመጽ ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ የሀገሪቱን ፓርላማ ከስራ ማገዳቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል።
በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ቱኒዚያውያን የሀገሪቱ መንግስት የኮቪድ 19ን የያዘበት መንገድ አግባብ አይደለም በሚል ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸው ይታወቃል።
በቱኒዝያ ዋና ከተማ ቱኒዝ እና በሌሎች ከተሞች ለተቃውሞ የወጡ የሀገሪቱ ዜጎች ለገዢው ፓርቲ ተቃውሞዋቸውን የገለጹ ሲሆን፤ የሀገሪቱ ፓርላማ እንዲበተንም ጠይቀዋል።
በተጨማሪም የሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ የሆነው ኤናድሃ ፓርቲ ጽህፈት ቤቶችን ሰብረው የገቡ ሲሆን፤ ኮምፒውተሮችን በመሰባበር በቢሮዎቹ ላይ እሳት መለኮሳቸው ተሰምቷል።
ኤናድሃ ፓርቲ ተግባሩን ያወገዘ ሲሆን፤ “በሀገሪቱ ሁከት እንዲፈጠር የሚፈልጉ ወንጀለኞች ተግባር ነው” ሲልም ገልጾታል።
የሀገሪቱ ፖሊስም በአመጸኞች ላይ አስለቃሽ ጭሶችን የተኮሱ ሲሆን፤ በርካታ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ዋማላቸውም ተሰምቷል።
አመጹ ከዚህ በኋላ የሚቀጥል ከሆነ ግን ወታደራዊ እርምጃዎች የሚወሰዱ መሆኑን የሀገሪቱ ፐሬዚዳንት ካይስ ሰይድ አስጠንቅቀዋል።
ፕሬዚዳንት ካይስ ሰይድ ሀገሪቱን ለማዳን እና ለማረጋጋት ሲባል ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሺም ማቺቺን ከስልጣን ማንሳታቸውን ገልጸዋል።
እንዲሁም የሀገሪቱ ህገ መንግሰት በሚፈቅድላቸው መሰረት የሀገሪቱን ፓርላማ ከስራ ማገዳቸውንም ነው ፐሬዚዳንቱ እለት ያስታወቁት።
ሆኖም ግን የፕሬዚዳንት ካይስ ሰይድ ተግባር “መፈንቅለ መንግስት ነው” ሲሉ ተቃውሞዋቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
የቱኒዚያ ፓርላማ አፈ ጉባዔም የፕሬዚዳንት ካይስ ሰይድ ተግባር በቱኒዚያ አብዮት እና ህገ መንግስት ላይ የተቃጣ መፈንቅለ መንግስተ ነው ሲሉ ተናገረዋል።