ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሜዲትራኒያንን ሲያቋርጡ የነበሩ 178 ስደተኞችን ከመስመጥ መታደጉን የቱኒዚያ ጦር አስታወቀ
የሶሪያና የደቡብ እስያ ስደተኞች ይገኙባቸዋልም ነው የተባለው
ስደተኞቹ ‘ዙዋራ’ ከተሰኘች የሊቢያ የባህር ዳርቻ ከተማ ተነስተው እጅግ አስቸጋሪውን የባህር ጉዞ መጀመራቸው ተነግሯል
የቱኒዚያ ባህር ኃይል ትናንት እሁድ በሊቢያ በኩል ሜዲትራኒያንን አቋርጠው ወደ አውሮፓ በመሻገር ላይ የነበሩ 178 ስደተኞችን ከመስመጥ መታደጉን አስታወቀ፡፡
ባህር ኃይሉ በደቡባዊ የሃገሪቱ ባህር ዳርቻዎች ባካሄዳቸው ሶስት ዘመቻዎች ስደተኞቹን በህይወት ለመታደግ መቻሉን አስታውቋል፡፡
ስደተኞቹ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከግብጽ፣ ከአይቮሪኮስት፣ ከናይጄሪያ፣ ከማሊ እና ከሶሪያ እንዲሁም ከባንግላዴሽ የተነሱ ናቸው፡፡
ዙዋራ ከተሰኘች የሊቢያ የባህር ዳርቻ ከተማ ተነስተው አርብ ሌሊቱን ለቅዳሜ አጥቢያ እጅግ አስቸጋሪውን የባህር ላይ ጉዞ መጀመራቸውም ነው የተነገረው፡፡
የቱኒዚያ ባለስልጣናት ባሳለፍነው ሃሙስ 267 በዋናነት ባንግላዴሻውያን ስደተኞችን መያዛቸውንም ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም (አይ.ኦ.ኤም) ገልጿል፡፡
አይ.ኦ.ኤም ሜዲትራኒያንን አቋርጠው አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩ በርካታ ስደተኞች መዳረሻቸው ደቡባዊ ቱኒዚያ የሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ሆነዋል ይላል መጠለያዎቹ መሙላት መጀመራቸውን በመጠቆም፡፡
በሊቢያ ያለው የከፋ ሁኔታ ስደተኞቹ ባህር እንዲያቋርጡ እያስገደዳቸው እንደሆነም ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የስደተኞች ኤጀንሲ ያስታወቀው፡፡
ተመድ ከጥር እስከ ግንቦት በነበሩት 5 ገደማ ወራት ሜድትራኒያንን ለማቋረጥ የሞከሩ የ760 ስደተኞች ህይወት ማለፉንም ገልጿል፡፡