ቱኒዚያ የተሳካ የአረብ አብዮት የተካሄደባት አገር ነበረች
የቱኒዚያው ፕሬዘዳንት ካይስ ሴይድ ባሳለፍነው እሁድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሂሼም ማቺቺን እና ፓርላማውን ከስራ ማገዳቸውን ተከትሎ በቱኒዝያ የፖለቲካ ውጥረት ተከስቷል።
በፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ ያለችው ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ቱኒዚያ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ሌሎች ባለስልጣናት በፕሬዘዳንቱ ከስራ ታግደዋል።
ፕሬዘዳንት ካይስ ሴይድ አሁን ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጸሀፊ እና አማካሪ ከስራ ማገታቸውን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት ካይስ ሰይድ ከኮቪድ 19 ሳቢያ በሀገሪቱ የተከሰተውን አመጽ ተከትሎ የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከኃላፊነት ማንሳታቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ በመላው ቱኒዚያ የተከሰተውን አመጽ ተከትሎ በያዝነው ሳመንት የሀገሪቱን ፓርላማ ከስራ ማገዳቸውም አይዘነጋም።
ይሁንና የፕሬዘዳንቱ ውሳኔ በቱኒዝያ የፓርላማ አባላት እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመቃወም ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
የቱኒዝያ ፓርላማ ቃል አቀባይ እንዳሉት የፕሬዘዳንቱ ውሳኔ ህጋዊ ያልሆነ እና መፈንቅለ መንግስት መሆኑን ተናግረዋል።
በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ቱኒዚያውያን የሀገሪቱ መንግስት የኮቪድ 19ን የያዘበት መንገድ አግባብ አይደለም በሚል ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸው ይታወቃል።
የዓረብ ጸደይ አብዮት መነሻየሆነችው ቱኒዚያ የተሳካ የዲሞክራሲ አብዮት የተካሄደባት በሚል ስትነሳ የቆየች ሲሆን አሁን ወደገጠማት የፖለቲካ አለመረጋጋት ወደከፋ ቀውስ ሊወስዳት ይችላል የሚሉ ስጋቶች በመነሳት ላይ ይገኛል።